Tuesday, April 28, 2015

የመስቀሉ ሕዝቦች

      (መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ሚያዝያ 20 ቀን 2007 ዓ.ም.)፡-በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
 በቅርቡ አይሲስ  የተባለው “ሃይማኖታዊ” ድርጅት “ክርስቲያን መግደል ገነት ያስገባል ፤ አላህ ደማቸውን እያየ ደስ ይለዋል” በሚል እንኳን መንፈሳዊነት ሰብአዊነት በጎደለው ፍፁም ሰይጣናዊ ትምህርት መነሻ በማድረግ ምንም የማያውቁትን ምስኪኖች በጭካኔ ግማሹን በተማሩት ትምህርት እንደበግ እያረዱ ግማሹን ደግሞ በጥይት እያርከፈከፉ ፈጅተዋቸዋል፡፡ በዚህም የኦርቶዶክሳውያን ልብ ፍፁም አዝኗል፤ አልቅሷል፡፡
ይሁን እንጂ ‹‹ መሳ ፲፬፡ ፰ - ፲፬ ከበላተኛው መብልን የሚያወጣ ››ጌታ ከእነዚህ አረመኔዎች አንድ አስደናቂ ቃል አሰምቶናል፡፡ ይኸውም እነዚህ አረመኔዎች ምስኪኖቹን ኦርቶዶክሳውያን ከማረዳቸው በፊት ሁሉንም በወል የጠሩበት ስም ‹‹ የመስቀሉ ሕዝቦች ›› የሚል ነው፡፡ መጽሐፍ  በ‹‹ዮሐ ፲፩ ፤ ፵፱ በዚያችም አመት የካህናት አለቃ የነበረው ስሙ ቀያፋ የተባለው ከእነርሱ አንዱ እንዲህ አላቸው ‹ እናንተስ ምንም አታውቁም ፤ ምንም አትመክሩም ሕዝቡ ሁሉ ከሚጠፋ  ስለ ሕዝቡ አንድ ሰው ቢሞት ይሻለናልና ›፡፡ ይህንም ከልቡ የተናገረ አይደለም ፤ ነገር ግን በዚያች አመት የካህናት አለቃ ነበርና ጌታችን ኢየሱስ ስለ ሕዝቡ ይሞት ዘንድ ስላለው ይህን ትንቢት ተናገረ፡፡››  እንደሚል ቀያፋን ክርስቶስ ለሰው ዘር በሙሉ በፈቃዱ ይሞት ዘንድ እንዳለው ትንቢት ይናገር ዘንድ ያደረገ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ፤ ዛሬም እነዚህን አረመኔዎች አፋቸውን ከፍቶ ፊታቸውን ጸፍቶ ስለ ኦርቶዶክሳውያን ያስመሰከራቸው ቃል እንጂ ወደው አስበው የተናገሩት አይደለም፡፡ ለዚህም አንዳንድ ማሳያዎችን ላቅርብ፡፡

መስቀል የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ሁለት አይነት ትርጓሜ አለው፡፡ የመጀመሪያው በቁሙ ከእንጨት ከብር ከወርቅ የሚሰራውናን ቅዱስ እቃ የሚመለከት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በምስጢራዊ ትርጉሙ ‹‹ተጋድሎ›› ተብሎ ይተረጓማል ፡‹‹ ማቴ ፲ ፡፴፰ መስቀሉንም ተሸክሞ እኔን በኋዬ የማይከተለኝ ለእኔ ሊሆን አይገባውም›› እንዲል፡፡ በሁለቱም ብንመለከተው  ‹‹ የመስቀሉ ሕዝቦች ›› የሚለው መጠሪያ ለኦርቶዶክሳውያን የተስማማ ነው፡፡
፩. በቁሙ መስቀል ሲሆን
መስቀል ማለት የተመሳቀለ ማለት ነው፡፡ በኦሪት አገልግሎቱ በተለይ በአሕዛብ ወንጀለኞችን ለመቅጣት ነበር፡፡ ወንጀለኞችን በመስቀል መቅጣት የተጀመረው በፋርሳውያን ሲሆን የተባለውን የምድር ‹‹አምላክ›› እንዳያረክስ እያሉ ወንጀለኞችን በመስቀል ይገድሉ ነበር፡፡ ይህ አሕዛባዊ ልማድ ሰልጥኖ እስራኤላውያንም ወንጀለኞችን በመስቀል የሚገድሉ ሆነዋል፡፡ በዚህ የተነሳ መስቀል የመርገም ምልክት ሆነ፡፡
ነገር ግን ጌታችን  አዳምን በፈቃዱ ሞቶ ለማዳን የመጣ ነውና ፤ ዛሬ ካህናቱ መስዋዕቱን በታቦቱ ላይ እንደሚሰዉ ፤ ጌታችንም በፈቃዱ በመስቀል ላይ ለአዳምና ለልጆቹ አንድ ግዜ መስዋዕት ሆኖ ከቀረበ በኃላ መስቀል የበረከት፤ የድል፤  የኦርቶዶክሳዊነት ምልክት ስለሆነ  ሐዋርያው ‹‹ገላ ፮፤፲፬ እኔ ግን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል እንጂ በሌላ አልመካም ›› ሲል፤ ንዑዳን ክቡራን የሆኑ ፫፻፲፰ቱ ሊቃውንት ደግሞ  ‹‹ መስቀል ኃይላችን ፤ መስቀል ቤዛችን ነው ፤ መስቀል የነፍሳችን መዳኛ ነው….›› የሚሉ ሆነዋል፡፡
ይህ ጌታችን የተሰቀለበት መስቀል እግዚአብሔር አባታችን ለኛ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ልጆች ሰጥቶናልና ‹‹ የመስቀሉ ሕዝቦች ›› ተብለን ልንጠራ ይገባናል፡፡ (ብዙ ግዜ የምንሰማው የቀኝ እጁ ብቻ እንዳለ ቢሆንም ገዳሙ ‹ አንብር መስቀልዬ በዲበ መስቀል › በሚል ያሳተመው መጽሐፍ ሙሉ መስቀሉ እንዳለ ይናገራል)፡፡ ‹ክርስቲያን› ነን ከሚሉ ከሌሎች የእምነት ድርጅቶች ተለይተን ለመስቀል የምንሰግድ ፣ ወር በገባ ፲ኛው ቀንና መስከረም ፲፮ በታላቅ ድምቀት መስቀል የምናከብር  ብቸኛ ክርቲያኖች ነንና ‹‹ የመስቀሉ ሕዝቦች ›› ተብለን ልንጠራ ይገባናል ፤ ብጹአን ጳጳሳት በአርዌ በትራቸው ፣ ቀሳውስቱ ከእጃቸው ለደቂቃ እንኳን ሳይለዩ እኛን ልጆቻቸውን ይባርኩበታልና  ‹‹ የመስቀሉ ሕዝቦች ›› ተብለን ልንጠራ ይገባናል ፤ መምህራኑ በመስቀልያ አጣፍተው በመስቀል ቅርጽ አማትበው በሚከፍቱት ቅዱስ ጉባኤ ቁጭ ብለን የምንማር ነንና ‹‹ የመስቀሉ ሕዝቦች ›› ተብለን ልንጠራ ይገባናል ፤ መስቀሉን በአንገታችን ከማሰር አልፈን በተለያዩ የሰውነታችን አካላት የምንነቀስ በልብሳችንም የምናስጠልፍ ኩሩ ሕዝቦች ነንና ‹‹ የመስቀሉ ሕዝቦች ›› ተብለን ልንጠራ ይገባናል ፤ በሰንበት ትምህርት አገልግሎት በመስቀል በተዋበ ጥንግ ድርብ በያሬዳዊ ዜማ ለልዑል እግዚአብሔር ምስጋና የምናቀርብ ልዩ ሕዝቦች ነንና ‹‹የመስቀሉ ሕዝቦች ›› ተብለን ልንጠራ ይገባናል ፤ በሮችዋና ጉልላቶችዋ በመስቀል በተጌጠች ቤተ ክርስቲያን በጥምቀት ልጅነት  ፣ በቁርባን ሕይወት ፤ በንስሀ ስርየተ ኃጢያት ያገኘን ነንና ‹‹ የመስቀሉ ሕዝቦች ›› ተብለን ልንጠራ ይገባናል ፤ በ እና ፹ ለተጠመቁ ልጆችዋ በመስቀል ቅርጽ ሜሮን እየቀባች የምታከብር ፣ በታመሙ ጊዜ በመስቀል ዳብሳ የምትፈውስ ፣ ባረፉም ጊዜ በመቃብራቸው ላይ መስቀል የምታኖር አንዲት ቅድስት ሐዋርያዊት ኩላዊት የሆነች ቤተ ክርስቲያን አባላት ነንና  ‹‹ የመስቀሉ ሕዝቦች ›› ተብለን ልንጠራ ይገባናል፡፡
፪. መስቀል ተጋድሎ መከራ ሲሆን
ከላይ እንደተገለጠው መስቀል ምስጢራዊ ትርጉሙ ተጋድሎ ማለት ነው፡፡ ተጋድሎ ማለት ደግሞ አንድ ኦርቶዶክሳዊ ሕገ እግዚአብሔርን ላለማፍረስ ከአጋንንት ከፍትወታት እኩያትና ከአላውያን ነገስታት ጋር የሚያደርገው ትግል ነው፡፡ በዚህም ትርጓሜ ብናየው አረመኔዎቹ እንዳሉት ‹‹ የመስቀሉ ሕዝቦች ›› ለኛ የሚገባ ስም ነው፡፡ ጌታችን በሐሙስ ምሽት ‹‹ማቴ.፳፮፡፴፱ ይች ጽዋ ከእኔ ትለፍ ›› ብሎ  ተጋድሎን ለቤተ ክርስቲያን ስላስተላለፈ እውነተኛዋ  ቤተ ክርስቲያን ያለተጋድሎ ልትኖር አትችልም፡፡ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ልጆችዋ መላ ዘመናቸው በተጋድሎ የሚያሳልፉ ናቸውና ‹‹ የመስቀሉ ሕዝቦች ›› ቢባሉ አያስደንቅም፡፡
አምላካቸው በገዳመ ቆሮንቶስ ቀንና ሌሊት በበረሓ ከአራዊቶች መኖሩን መማሰብ በየጫካው በበረሓው ድምጸ አራዊቱን  ግርማ ሌሊቱን ፣ የቀኑን ሐሩር የሌሊቱን ቁር ታግሰው የሚበላውንና የሚጠጣውን ንቀው ፣ ካማረና ከደመቀ ልብስ ተራቁተው ፣ እድሜ ዘመናቸውን በጾም በጸሎት በስግደት እየተጋደሉ የሚኖሩ መነኮሳት ልጆች ነንና ‹‹ የመስቀሉ ሕዝቦች ›› ተብለን ልንጠራ ይገባናል ፤ አብነት መምህራኖችዋና ተማሪዎችዋ ረኃቡን ጥሙን ታግሰው ፣ ‹‹ሰርተህ አትበላም›› የሚለውን ነቀፌታ የውሻውን ንክሻ ችለው ፣ የቤተሰቦቻቸው ናፍቆት እናዳያሸንፋቸው እየተጋደሉ በመማርና በማስተማር ለቅድስና የሚበቁባት ቤተ ክርስቲያን አባላት ነንና ‹‹ የመስቀሉ ሕዝቦች ›› ተብለን ልንጠራ ይገባናል ፤ ራሳቸውን ከዓለም ርኩሰት ለይተው እድሜ ዘመናቸው ሁሉ በድንግልና በመኖር ከፍትወታት እኩያት ጋር የሚጋደሉ የእውነተኞቹ ጳጳሳት ልጆች ነንና ‹‹ የመስቀሉ ሕዝቦች ›› ተብለን ልንጠራ ይገባናል ፤ እኛ ኦርቶዶክሳውያን ከ፫፻፷፭ ቀናት መካከል ከ፪፻ ቀናት በላይ በጾም ከጥሉላት መባልዕትና ከሩካቤ ስጋ የምንርቅ የተጋድሎ ሕዝቦች ነንና ‹‹ የመስቀሉ ሕዝቦች ›› ተብለን ልንጠራ ይገባናል፡፡
በመጨረሻ፡- መጽሐፍ ‹‹ ሐዋ ፲፩ ፤ ፳፰  ደቀ መዛሙርትም መጀመርያ በአንጾኪያ ክርስትያን ተብለው ተጠሩ›› ይለናል፡፡ ይህ የከበረ ስም የተሰጠን በራዕይ ወይም በጉባዔ ተወስኖ አይደለም፡፡ ይልቁንም አምላካችን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ይንቁና ያንቋሽሹ የነበሩ አይሁድ ‹‹ የዛ የእንጨት ጠራቢው የዮሴፍ ልጅ ፣ አጋንንት በአጋንንት ያወጣ የነበረው ፣ ሳይሆን ራሱን ይመጣል የተባለው መሲህ ክርስቶስ እኔ ነኝ ይል የነበረው ፣ ነገር ግን ሞቶ የቀረው ሰው ›› (ሎቱ ስብሐት) ተከታዮች ናቸው ለማለት ሐዋርያትንና የመጀመርያዎቹን ክርስቲያኖች ለመንቀፍ ያወጡልን ስም ነበር፡፡ ነገር ግን አይሁዳውያኑ ሳይገባቸው (‹ባ› ላልቶ ይነበባል) ያወጡልን ስም ለሐዋርያት ስለተመቻቸው (ክርስቲያን ማለት የክርስቶስ ተከታይ ማለት ነውና) ‹‹ክርስቲያን›› የሚለውን መጠሪያቸው አድርገው አፅንተውታል፡፡ ዛሬም ኣረመኔዎቹ ሳይገባቸው ‹‹የመስቀሉ ሕዝቦች ›› ብለው የሚገባንን ስም አውጥተውልናል ፤ ስሙም ተመችቶናል፡፡ ከዚህ በኃላ በጥምቀት በመስቀልና በታላላቅ በዓላቶቻችን ሰማዕታቱን ለማዘከርና ስሙም ስለተመቸን ‹‹ የመስቀሉ ሕዝቦች ›› የሚለውን ስም እንደ ኣዲስ እናስተዋውቀዋለን ፤ እንጠራራበታለን፡፡    
  የሰማዕታቱ በረከት ይደርብን ፤ እኛንም በሃይማኖት በምግባር ያጽናን !!!!!
                            የእናታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ምልጃ አይለየን፡፡                                                                             
                                                                               ዳዊት ተስፋይ
                                                     ከተክለ ሳዊሮስ ሰ/ት/ቤት

2 comments:

  1. አዎ ነን አምላክ አጆቸህን ይባርካቸው

    ReplyDelete

FeedBurner FeedCount