Thursday, April 30, 2015

ስለ ጌጠኛ ልብስ

በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ

(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ሚያዝያ 22 ቀን፣ 2007 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
ዕርቃናችንን የምንሸፍንበት ልብስ ብቻ ልንለብስ ይገባናል፡፡ ብዙ ወርቅን ብናደርግ ምንድነው ትርጉሙ? ብዙ ወርቅን ማድረግ በተውኔት ቤት ነው፤ ተዋንያን ብዙ ተመልካችን ለማግኘት ያደርጉታልና፡፡ ጌጠኛ ልብስ መልበስ የአመንዝራ ሴቶች ግብር ነው፤ ብዙ ወንዶች ይመለከቷቸው ዘንድ ይኽን ያደርጋሉና፡፡ እነዚኽን ማድረግ ልታይ ልታይ ለሚሉ ሰዎች ነው፡፡ እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት የምትሻ ሴት ግን ይኽን ጌጥ ማድረግ አትፈልግም፡፡ ራሷን የምታስጌጠው በሌላ መንገድ ነው፡፡ እናንተም ይኽን ጌጥ ማድረግ የምትፈልጉ ከኾነ ማድረግ ትችላላችኁ፡፡ ተውኔት ቤትን የምትሹ ከኾነም ወርቀ ዘቦአችኁን የምታደርጉበት ሌላ ተውኔት ቤት አለላችኁ፡፡ ያ ተውኔት ቤትስ ምንድነው? መንግሥተ ሰማያት ነው፡፡ ተመልካቾቹ ቅዱሳን መላእክት ናቸው፡፡ ይኽን የምናገረው በገዳም ለሚኖሩት መኖኮሳይያት ብቻ አይደለም፤ በማዕከለ ዓለም ለሚኖሩትም ኹሉ ጭምር እንጂ፡፡ በክርስቶስ ክርስቲያን በወልድ ውሉድ የተባለ ኹሉ የራሱ ተውኔት ቤት አለው፡፡ ስለዚኽ ተመልካቾቻችንን ደስ ለማሰኘት ራሳችንን ደኅና አድርገን እናጊጥ ብዬ እማልዳችኋለኁ፡፡ ለመድረኩ የሚመጥን ልብስን እንልበስ፡፡ እስኪ ንገሩኝ! አንዲት ሴሰኛ ሴት ተውኔት ለመሥራት ብላ ብዙ ወርቋን አወላልቃ፣ ቄንጠኛ መጎናጸፍያዋን ጥላ፣ በሳቅ በስላቅ ሳይኾን ቁም ነገርን ይዛ፣ ተርታ ልብስን ለብሳ ወደ መድረኩ ብትወጣና ሃይማኖታዊ ንግግርን ብትናገር፣ ስለ ንጽሕና ስለ ቅድስና ብትናገር፣ ሌላ ክፉ ንግግርም ባትጨምር በተውኔት ቤቱ የሞላው ሰው አይነሣምን? ተመልካቹ ኹሉ የሚበተን አይደለምን? ሰይጣን የሰበሰበው ተመልካቹ የማይፈልገውን ነገር ይዛ ስለ መጣች ኹሉም የሚሳለቅባትና እንደ ትልቅ አጀንዳ የሚወራላት አይደለምን? አንተም በብዙ ወርቅ፣ በጌጠኛ ልብስ ተሸላልመኽ ወደ መንግሥተ ሰማያት ብትገባ ቅዱሳን መላእክት አስወጥተው ይሰዱኻል፡፡ ምክንያቱም በመንግሥተ ሰማያት የሚያስፈልገው ልብስ እንደዚኽ ዓይነት አይደለም፤ ሌላ ነው እንጂ፡፡ “ርሱስ ምን ዓይነት ነው?” ትለኝ እንደኾነም “ነፍስን በትሩፋት ማስጌጥ ነው” ብዬ እመልስልኻለኁ፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ክቡር ዳዊት፡- “ልብሷ የወርቅ መጐናጸፍያ ነው” ያለውም ይኽንኑ ነው እንጂ በዚኽ ምድር የምንለብሰው ልብሳችንን ፀዓዳና አንጸባራቂ ስለ መኾን አይደለም /መዝ.45፡13/፡፡ ምክንያቱም “ለሐሴቦን ንጉሥ ልጅ ኹሉ ክብሯ ነው” እንዳለ በዚያ (በመንግሥተ ሰማያት) መራሔ ተውኔቷ ርሷ ናት፡፡ እኅቴ ሆይ! ራስሽን መሸላለም ብትፈልጊ እንዲኽ አጊጪ፡፡ ከዚያም ከምረረ ገሃነም ትድኛለሽ፡፡ ባልሽንም ከማዘን ከመቆርቆር ትታደጊዋለሽ፡፡

ባልሽ እጅግ ደስ የሚሰኘው እንዲኽ ስታጌጪ ነው፡፡ ምክንያቱም ብዙ ወንዶች ሚስቶቻቸው “ሥጋችንን እናጊጥ” ሲሏቸው ደስ አይላቸውም፡፡ እንዲኽ በሚያዘወትሩ ሚስቶቻቸውም ያፍራሉ፡፡ ከክብረ ሥጋ ይልቅ ክብረ ነፍስን የምታስቀድሙ ከኾነ ግን ገንዘብ ስጡን ስለማትሏቸው ሰጠናቸው ብለው ከመታበይ ይድናሉ፡፡ እኔ እበልጥ የሚል ስሜታቸው ይወገዳል፡፡ ምድራዊ ወርቅን እንደማትፈልጊና ለዚያ መግዣ የሚኾን ገንዘብ ሳትጠይቂው ሲመለከት እጅግ ቁጡ ቢኾንም አጊጠሸ ከሚያከብርሽ በላይ ሳታጌጪ ያከብርሻል፡፡ አንቺም የርሱ ተገዢ አትኾኚም፡፡ የሰው ተገዢ የምንኾነው ከዚያ ሰውዬ ብዙ ነገርን የምንሻ ከኾነ ነውና፡፡ በዚኽ ዓለም ሐላፊና ጠፊ ነገር ግድም እንደሌለን ሲያውቅ ግን ያ ሰው እኛ ላይ የሚሠለጥንበት ምክንያት የለውም፡፡ በመኾኑም እንደዚኽ ስትኾኚ ባልሽን የምትታዘዢው ጊዜአዊ ነገር ስለ ሰጠሸ ሳይኾን እግዚአብሔርን ፈርተሸ እንደኾነ ይገነዘባል፡፡ ከዚኽ በኋላ አንድ ነገር ስላደረገልሽ ብታመሰግኚው እንኳን የሰጠሸው ክብር ስላደረገው ነገር እንዳልኾነ ይረዳል፡፡ አንቺ በምላሹ የሰጠሽው ነገር ትንሽ ቢኾንም ትንሽ ነው ብሎ አይቈጥረዉም፡፡ ወይም አይበሳጭም፡፡
በብዙ ወርቅ መሸላለምና ጌጠኛ ልብስን ለብሶ በአደባባይ ከመዞር በላይ ምን ስንፍና አለ? በአደባባይስ ብዙ ባልደነቀኝ፤ እንዲኽ ተሸላልማ ወደ ቤተ ክርስቲያን የምትመጣ ግን እጅግ ሰነፍ ናት፡፡ “በሽሩባና በወርቅ ወይም በዕንቁ ወይም ዋጋው እጅግ በከበረ ልብስ አይሸላለሙ” የሚለውን /1ኛ ጢሞ.2፡9/ ቃል መስማት ሲገባት እንዲኽ አጊጣና ተሸላልማ የምትመጣው ምን ለማድረግ ነው? አንቺ ሴት እስኪ ንገሪኝ! ምን ለማድረግ ነው የመጣሽው? ከቅዱስ ጳውሎስ ጋር ጠብ ለመግጠም ነውን? እልፍ ጊዜ እንዲኽ አትልበሺ ብሎ ቢነግርሽም ንቀሽው መምጣትሽ ምን ለማድረግ ነው? ወይስ ቅዱስ ጳውሎስን መስለን እንዲኽ የምናስተምረው መምህራን ትምህርቱን በከንቱ እንዳስተማርን ዐይተን እንድናፍር ሽተሸ ነው? አንቺ ሴት እስኪ ንገሪኝ! አንድ እነዚኽን የቅዱስ ጳውሎስ ቃላት የሰማ ኢአማኒ ባል “በወርቅ ወይም በዕንቁ ወይም በከበረ ልብስ አይሸላለሙ” የሚለውን የሐዋርያው ቃል ለመስማት ወደ ቤተ ክርስቲያን ለመሔድ የምትዘጋጀውን ክርስቲያን ሚስቱ ራሷን በብዙ እንደምትሸላልም፣ ጌጠኛ ልብስን እንደምታደርግ ቢያያት ምንድነው የሚለው? “ባለቤቴ ምን እየሠራች ነው? በመስታወቱ ፊት ይኽን ያኽል ሰዓት መቆየቷ ስለምንድነው? ይኽን ያኽል ወርቅ መልበሷ ለምንድነው? መሔድ ያሰበችው ወዴት ነው? ወደ ቤተ ክርስቲያን ነውን? ምን ለማድረግ? በወርቅ ወይም በዕንቁ ወይም በከበረ ልብስ አይሸላለሙ የሚለውን ቃል ለመስማት ነውን?” እያለ ብዙ አይዘብትምን? ብዙ አይሳለቅምን? ሃይማኖታችን ስላቅና ማታለል እንደኾነች አያስብምን? ስለዚኽ እማልዳችኋለኁ! ጌጠኛ ልብስን ለወታደራዊ ሰልፈኞች፣ ለተውኔት ቤቶች፣ ልብስን ለሚሸጡ እንተውላቸው፡፡ ትዕቢት እና ውዳሴ ከንቱ በሌለበት በምግባር በትሩፋት እናጊጥ እንጂ በእኛ ውስጥ ያለውን የእግዚአብሔር መልክ በእነዚኽ ጌጦች አንሸፍነው፡፡ እኅቴ ሆይ! ከወንዶች ክብርን ማግኘት ሽተሸ እንደኾነ በዚኽ ታገኚዋለሽና የክርስቶስን መልክ አትሸፍኚው፡፡ ምክንያቱም እኛ ወንዶች ባለጸጋ ሴት ብዙ ብታጌጥ አይደንቀንም፡፡ የሚደንቀን ባለጸጋ ኾና ሳለ ዕርቃኗን ለመሸፈን ብቻ ብላ ተርታ ልብስን ለብሳ ስትሔድ ብንመለከት ነው፡፡ እኛ ብቻ አይደለንም፤ ጻድቃን ኹሉ የሚያደንቋት ዘማውያን የሚጠሏት ይኽቺን ሴት ነው፡፡ ጌጠኛ ልብስን እንዲኹም ወርቅን የሚያደርጉ ሴቶች ብዙ ናቸው፡፡ አንዲቱን ልብለጣት ብትል ሌላኛዋ ነገ ሌላ ጌጥ ይዛ ስለምትመጣ ትበልጣታለች፡፡ በመኾኑም ኹሉንም ልብለጣቸው ስትል እንደ ንግሥቲቱ የወይራ ጉንጉን በራሷ ላይ ልታደርግ ትችላለች፡፡ ነገር ግን እጅግ የምታስደንቀውና ከእነዚኽ ሴቶች ኹሉ (ከንግሥቲቱም ጭምር) ይልቅ እጅግ ያጌጠችው ተርታ ልብስ የለበሰቿ ናት፡፡ ከእነዚኽ ኹሉ ሴቶች ይልቅ እጅግ የከበረችውም ርሷ ናት፡፡
ነገር ግን ይኽንን የምናገረው ባል ለሌላቸው እና ለባለጸጎች ሴቶች ብቻ አይደለም፤ ባል ላላቸው ሴቶችም ጭምር እንጂ፡፡
“ተርታ ልብስን ብለብስ ባለቤቴን ደስ ላሰኘው አልችልም” ትዪኝ እንደኾነም እንዲኽ ብዬ እመልስልሻለኁ፡- “እንዲኽ የምታጌጪው ባልሽን ደስ ለማሰኘት አይደለም፤ ልብስ በሌላቸው ድኾች ሴቶች ልትመኪ ወደሽ ነው እንጂ፡፡ ልቡናቸውን በቅንአት እንደ ሰም ታቀልጪ ዘንድ ሽተሸ ነው እንጂ፡፡ በድኽነታቸው እንዲያማርሩና ኀዘናቸውን ልትጨምሪባቸው ፈልገሽ ነው እንጂ፡፡” አንቺ ሴት! በአንቺ ምክንያት እግዚአብሔርን ይሰድቡ ዘንድ ምን ያኽል ምክንያት እንደኾንሻቸው ታስተውያለሽን? “ስለምን ድኾች ኾንን? እግዚአብሔር ድኾችን አይወድም፡፡ ድኽነትን የሚያመጣባቸው ለማይወዳቸው ሰዎች ነው” እንዲሉ እንደምታደርጊያቸው ትገነዘቢያለሽን? አዎ! ጌጠኛ ልብስ የማድረግሽ ዓላማ ባልሽን ደስ ለማሰኘት አይደለም፡፡ ባልሽን ደስ የማሰኘት ዓላማ ቢኖርሽ ኖሮስ ከቤትሽ ስትወጪ ያደረግሽውን ወርቅና ዕንቁ እንዲኹም ጌጠኛ ልብስሽን ከቤትሽ ስትገቢ ፈጥነሽ ባላወለቅሺው ነበር፡፡ ስለዚኽ ባልሽን ደስ ማሰኘት የምትፈልጊ ከኾነ ሌላ ብዙ መንገድ አለ፡፡ በትሕትናሽ፣ በየውኀትሽና በርኅራኄሽ ባልሽን ደስ አሰኚው፡፡ አንቺ ሴት እመኚኝ! ባልሽ ምንም ያኽል ዕውቀት የሌለው ቢኾን እንኳን እንዲኽ እንደነገርኩሽ ብታጌጪ ቅዱስ እንዲኾን ማድረግ ይቻልሻል፡፡ ምንም ያኽል ትምክሕተኛ፣ ትዕቢተኛ እንዲኹም አባካኝ ቢኾንም ከዚኽ የተለየ እንዲኾን ማድረግ ይቻልሻል፡፡ አንቺ እንደምታስቢው ባልሽን ደስ ለማሰኘት ብለሽ በአፍአ ብዙ ብታጌጪ ግን ከእነዚኽ ክፉ ምግባራት የተለየ እንዲኾን ማድረግ አይቻልሽም፡፡ የምናገረው ነገር ለጊዜው ላይገባሽ ይችላል፡፡ እንዲኽ እንደነገርኳችኁ በማድረጋቸው ባላቸውን ደስ ያሰኙት ግን ያውቁታል፡፡ ልዩ ልዩ ጌጣጌጦችን አድርጋችኁ ራሳችኁን ብታቆነጃጁ ግን ባለቤታችኁ ዘማዊ ከኾነ ከእናንተ ይልቅ በተሻለ ጌጥ ወዳጌጠችው ይሔዳል፡፡ ባልሽ ንጹሕ ከኾነ ግን ጌጠኛ ልብስ በመልበስ ደስ አታሰኚውም፤ በበጎ ምግባርሽ እንጂ፡፡ እንደዉም እንዲኽ ርሱን ደስ አሰኘዋለኁ ባልሽው ተግባር ይበልጥ እንደምታሳዝኚው በእውነት እነግርሻለሁ፡፡ ከእግዚአብሔር ይልቅ ይኽን ዓለም እንደምትወጂ ያስባል፡፡ ምንም ያኽል በጎ ሕሊና ቢኖረዉም መናገር አፍሮ በልቡ ይጠረጥርሻል፡፡ ቅናተኛ እንዲኾን ታደርጊዋለሽ፡፡ እንዲኽ በማድረግሽ ከርሱ ማግኘት የነበረብሽን ደስታ ታጫለሽ፡፡ ይኽም ብቻ አይደለም፤ ትፋቻለሽ፡፡
ምናልባት በምናገረው ነገር ተበሳጭታችኁ “ለወንዶች አግዞ ሴቶች እንዳያጌጡ ይቃወማል”  ልትሉኝ ትችላላችኁ፡፡ ነገር ግን አይደለም፡፡ ወንድ ስለኾንኩኝ ለወንዶች አድልቼ አይደለም፡፡ እንዲኽ አድርጌ የምናገረው እናንተው ራሳችኁ ትዳራችኁን እንዳታፈርሱ ብዬ ነው፡፡ ከሐላፊና ጠፊ ግብር እንድለያችኁ ብዬ ነው፡፡
አምራችኁ አጊጣችኁ መታየትን ትወዳላችኁን? እኔም እግዚአብሔር በሚወደውና ሰማያዊው ንጉሥ በመረጠው መንገድ ታጌጡ ዘንድ እወዳለኁ /መዝ.45፡11/፡፡ እኅቴ ሆይ! እስኪ ንገሪኝ፤ የትኛው ትመርጫለሽ? እግዚአብሔር እንዲወድሽ ነውን ወይስ ሰው ይወድሽ ዘንድ ነው? በምግባር በትሩፋት ብታጌጪ እግዚአብሔር ይወድሻል፡፡ ጌጠኛ ልብስን ብትወጂ ግን ዘማውያን ይወዱሻል፤ አንድም እግዚአብሔር ይጠላሻል፡፡ እግዚአብሔር የሚወደው ጌጠኛ ልብስን ሳይኾን ጌጠኛ ነፍስን ነው፡፡ ዘማውያን ግን ጌጠኛ ነፍስን ሳይኾን ጌጠኛ አፍአዊ ሰውነትን ይወዳሉ፡፡ እናንተ ሴቶች ሆይ! እንግዲኽ ከወንዶች ይልቅ እናንተን እንደወደድኳችኁ፣ በእውነተኛው ትሩፋት ታጌጡ ዘንድ እንደምደክም፣ ዘማውያን ከሚወዷችኁ እግዚአብሔር እንዲወዳችኁ እንደምተጋ አስተዋላችኁን? እግዚአብሔር የሚወዳት ሴትስ ምን ትመስላለች? መላእክትን ትመስላለች፡፡ አንድ ምድራዊ ንጉሥ የሚወዳት ሴት ከኹሉም ይልቅ ደስ ከኾነች ልዑል እግዚአብሔር ፈጽሞ የሚወዳት’ማ ክብሯ እንደምን ይበዛ ይኾን? ዓለሙን ኹሉ እስከ ምጽአት ድረስ ስትገዢ ብትኖሪ ይኽን ክብር የሚተካከል የለም ብዬ በእውነት ያለ ሐሰት እነግርሻለኁ፡፡
እንግዲያው ወንድሞቼ ሆይ! ማለፍ መለወጥ በሌለባት በመንግሥተ ሰማያት ጸጋንና ክብርን እናገኝ ዘንድ በምግባር በትሩፋት እናጊጥ፡፡ በዚኽ ዓለም የሚኖረን ውበትና ጌጥ ድንገት ታይቶ የሚጠፋ ነው፡፡ የማይቻል ቢኾንም ምንም በሽታ፣ ኀዘን፣ ብስጭት፣ ይኽም የመሳሰለ ኹሉ ባያገኘን እንኳን የዚኽ ዓለም ውበትና ጌጥ ሃያ ዓመት ነው፡፡ በወዲያኛው ዓለም የሚሰጠው የሚገኘው ክብር ግን በዝቶ ሲሰጥ ይኖራል እንጂ መቼም መች አያልፍም፡፡ አይለወጥም፡፡ እርጅና የለምና ቆዳው አይጨማደድም፡፡ ደዌ ሥጋ ደዌ ነፍስ አያገኘውም፡፡ ኀዘን አያወይበውም፡፡ በዚያ የምናገኘው ክብር፣ ውበት፣ ጌጥ ከዚኽ ኹሉ የተለየ ነው፡፡ በዚኽ ዓለም የምናገኘው ክብርና ውበት ግን የሚጠፋው ገና ከመምጣቱ ነው፡፡ ቢመጣ እንኳን አድናቂዎቹ ብዙ አይደሉም፡፡ ትሩፋትን ጌጥ ያደረጉ ሰዎች አያደንቁትም፡፡ የሚያደንቁት አመንዝሮች ናቸው፡፡
ስለዚኽ ከዚኽ ዓለም ከኾነው ክብር ልንለይ ይገባናል፡፡ መንግሥተ ሰማያትን እንወርስ ዘንድ ልንፈልገው የሚገባን ትሩፋትን ነው፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር!!!

7 comments:

  1. ይህን የመሰለ ግሩም ትምህርት በተለይ በዚህ ዘመን በጣም አስፈላጊ ስለሆነ በርቱ ። እግዚአብሔር ዋጋችሁን በከብር ፣በሞገስ ፣በፀጋ ይክፈላችሁ ።

    ReplyDelete
  2. አሜን ቃለ ህይወት ያሰማልን

    ReplyDelete
  3. አሜን ቃለ ህይወት ያሰማልን

    ReplyDelete
  4. አሜን ቃለ ህይወት ያሰማልን

    ReplyDelete
  5. ቃለ ሕይወትን ቃለ በረከትን ያሰማልን በዕድሜ በጸጋ ይጠብቅልን ውድ የመቅረዝ ተከታታዮች/ እንዲሁም አባቶቼ አንድ ጥያቄ አለኝ እርሱም የምትለቋቸውን ትምህርቶች እንዴት ይደርሱኛል ማለት አሁን መቅረዝ ብየ ጽፌ ነው የማገኘው እኔ ልል የፈለግኩት እናንተ ትምህርቱን ስትልኩት ለእኔ ወዲያው የሚደርሰኝ እንዴት ብሎ ነው እባካችሁ አስረዱኝ በእግዚአብሔር ስም

    ReplyDelete

FeedBurner FeedCount