Monday, April 13, 2015

ትምህርተ ሃይማኖት (ክፍል ዘጠኝ)

(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ሚያዝያ 6 ቀን፣ 2007 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
        ክርስቶስ ተንሥአ እሙታን - በዐቢይ ኃይል ወሥልጣን
        አሰሮ ለሰይጣን - አግዐዞ ለአዳም
        ሰላም - እምእዜሰ
        ኮነ - ፍሰሐ ወሰላም
        ውድ የመቅረዝ አንባብያን! እንዴት አላችኁ? የትምህርተ ሃይማኖት ትምህርቱን እየተከታተላችኁ እንደኾነ ጽኑ እምነቴ ነው፡፡ እስከ አኹን ድረስ የትምህርተ ሃይማኖት መግቢያ፣ የሃይማኖት አዠማመርና እድገት፣ ከኹሉም በፊት አንድ ኦርቶዶክሳዊ ክርስቲያን ማወቅ ያለበት ብለን ነገረ ቤተ ክርስቲያን፣ ቅዱስ ትውፊት፣ ኦርቶዶክሳዊ የመጽሐፍ ቅዱስ አረዳድ፣ ስለ ዶግማና ቀኖና፤ ስለ እግዚአብሔር መኖርና ስለ ባሕርዩ ጠባያት እንዲኹም ስሙ ማን እንደኾነ ተማምረናል፡፡ ዛሬም ሥነ ፍጥረት ብለን እንቀጥላለን፡፡ እግዚአብሔር ማስተዋልን ያድለን፡፡ አሜን!!!

ሥነ ፍጥረት
ትርጕም
የፍጥረት መበጀት፣ የተዋበ ፍጥረት /ዘፍ.1፡31/፤ አንድም የፍጥረት መስማማት፣ የተስማማ ፍጥረት ማለት ነው፡፡ አራቱ ባሕርያት በባሕርያቸው የማይስማሙ ቢኾኑም በእግዚአብሔር ጥበብ ይስማማሉና፡፡
የሥነ ፍጥረት ትምህርትን የመማር ጠቀሜታ
1.     የእግዚአብሔርን ፈጣሪነት፣ ጥበብ፣ ኹሉን ቻይነት፣ መጋቢነት፣ ከምንም በላይ ደግሞ ለሰው ያለውን ፍቅር የምንረዳባቸው ናቸው፡፡ የኦሪት ዘፍጥረት የመዠመሪያውን ምዕራፍ ስናጠና፥ እግዚአብሔር አባት እንደመኾኑ ለሚወደው ልጁ ምድርንና በርሷ ውስጥ ያሉትን ፍጥረታት ለመብል፣ ለአንክሮና ለተዘክሮ፣ በተልዕኮ እንዲያገለግሉት እንዳዘጋጀለትና በርሷ ላይ እንደሾመው እንገነዘባለን፡፡
2.    እግዚአብሔር የሥራ አምላክ መኾኑን እንረዳባቸዋለን፡፡
3.    የፍጥረት አስገኚ እግዚአብሔር ብቻ እንደኾነ ዐውቀን ከስሕተት ትምህርት እንድንጠበቅ ይረዱናል፡፡ በፈረንሳይ ሀገር የሚኖር አንድ እግዚአብሔር የለሽ ክፉና በእግዚአብሔር አማኝ ላይ የሚቀልድ ሰው ነበር ይባላል፡፡ ከዕለታት በአንዱ ቀንም ከአንድ አማኝ ገበሬ ጋር ተገናኝተው ሲጨዋወቱ ያ ክፉ ሰው አማኙን ገበሬ ይጠይቀዋል፡፡ “አኹን ስለ እግዚአብሔር የሚያወሩ የአምልኮት መጻሕፍቶችኅን ኹሉ ብቀዳቸው በምን ታመልካለኅ?” አለው፡፡ ገበሬውም “ሰማይን ከነግሱስ ቀደኅ ትጥልብኝ ይኾን?” ብሎ በአንክሮ ለፌዘኛው እግዚአብሔር የለሽ መለሰለት ይባላል፡፡ ስለ እግዚአብሔር ህልውና መጻሕፍት ብቻ ሳይኾኑ ፍጥረታትም ኹሉ ይመሰክራሉና፡፡
4.    ከዚኽም በላይ ደግሞ እነዚኽ በዘፍጥረት አንድ ላይ የተጠቀሱት ፍጥረታት በሙሉ መንፈሳዊ ትርጓሜ አላቸውና ከእነዚኽ እንድንማር ነው፡፡ ለምሳሌ የፍጥረታት አስገኚ በውኃ ላይ ይሰፍ የነበረው መንፈስ ቅዱስ እንደኾነ ኹሉ እኛም ዳግም ከውኃና ከመንፈስ ተወልደን የእግዚአብሔር ልጆች ልንኾን እንደሚገባ ያስገነዝባል፡፡ ይኽን የመሰለ ብዙ ትርጓሜ አለው፡፡
እግዚአብሔር ፍጥረትን የፈጠረበት ዓላማ
1.     ሰዎችና መላዕክት ስሙን ቀድሰው ክብሩንና መንግሥቱን እንዲወርሱ /ኤፌ.2፡10/፤
2.    የህልውናው መታወቂያ እንዲኾኑ /መዝ.100፡3፣ ሐዋ.14፡17፣ ሮሜ.1፡19-20፣ ዕብ.11፡1-3/፤
3.    ምግበ ሥጋ (አዝርዕቱ፣ አትክልቱ፣ ፍራፍሬው፣…)፣ ምግበ ነፍስ (ስንዴው ለቅዱስ ሥጋው፣ ወይኑ ለክቡር ደሙ፣ ዕጣኑ ለመሥዋዕቱ) እንዲኾኑ፤
4.    መማሪያ ማስተማሪያ እንዲኾኑ፡፡ ለምሳሌ ፀሐይ የምሥጢረ ሥላሴ፣ የብርሃንና የዓይን መዋሐድ የምሥጢረ ሥጋዌ፣ የፀሐይ መውጣትና መግባት የምሥጢረ ትንሣኤ ሙታን መማሪያ ናቸው፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ በሥነ ፍጥረት የመዠመሩ ምሥጢር
መጽሐፍ ቅዱስ በሥነ ፍጥረት መዠመሩ ስለ ብዙ ምክንያት ነው፡፡ ከእነዚኽም መካከል፡-
1.     እስራኤላውያን ወደ ግብጽ በመሰደዳቸው ምክንያት ለ430 ዓመታት በአሕዛብ መካከል ኖረዋል፡፡ በዚኽም አምልኮ ጣዖትን ተለማምደው ነበር፡፡ በልቡናቸው ሰሌዳነት ተጽፎ የነበረውን ሕገ እግዚአብሔር ረስተዉት ነበር፡፡ በመኾኑም ይኽን ወደ ቀጣዩ ትውልድ እንዳያስተላልፉት በማሰብ እግዚአብሔር በነቢዩ ሙሴ አድሮ ትክክለኛውን ነገራቸው /ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ፣ የኦሪት ዘፍጥረት ትርጓሜ ገጽ 67-68/፡፡
2.    እግዚአብሔር እንዲኽ ፈጣሪነቱን በጽሑፍ ማስቀመጡ የሰው በደል ባመጣው ድካም ነው፡፡ እግዚአብሔር ሰውን ማናገር የሚፈልገው በጽሑፍ አልነበረም፡፡ እግዚአብሔር የሚፈልገው ከልጆቹ ጋር አፍ ለአፍ መነጋገርን ነው፡፡ የበለጠ የምንረዳውም እንዲኽ ሲያናግረን ነው፡፡ አዳምን ያናገረው እንዲኽ ነበር፡፡ ቃየንን የዘለፈው እንዲኽ ነበር፡፡ ከኖኅ ጋር የተነጋገረው፣ በአብርሃም ቤት የተስተናገደው እንዲኽ አፍ ለአፍ በመነጋገር ነበር፡፡ የሰው ልጅ በክፋት ዐዘቅት ቢወድቅም እንኳን ከሰው ልጆች አልራቀም ነበር፡፡ ሰው ግን አብዝቶ ከእግዚአብሔር እየራቀ መጣ፡፡ ከጣዖታት ጋር ተዛመደ፡፡ ሰው ወዳጁ እግዚአብሔርም ፍቅሩን ማደስ ፈለገ፡፡ ከእኛ ርቆ ለሚገኝ ሰው እንደምናደርገውም ከርሱ ርቆ ወደ ሔደው ሰው ደብዳቤ ላከ፡፡ ደብዳቤውም ፍቅራችንን እናድስ የሚል ነበር፡፡ እግዚአብሔር ደብዳቤውን ወደ ሰው የላከው በሙሴ አማካኝነት ነበር፡፡ ሲዠምርም “በመዠመሪያ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ፈጠረ” ይላል /ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ፣ የኦሪት ዘፍጥረት ትርጓሜ፣ ድርሳን 2/፡፡ 
3.    በጥንታዊቱ ቤተ ክርስቲያን የነበሩት ከሐዲያን (ለምሳሌ ግኖስቶኮች) ከሥነ ፍጥረት አንጻር የነበራቸው አመለካከት “ግዙፉ ዓለም ከመንፈሳዊው ዓለም ጋር ምንም ግንኙነት የለውም” የሚል ነበር፡፡ እግዚአብሔር ግን በሙሴ አድሮ እንደፈጠራቸው ብቻ ሳይኾን “ኹሉም መልካም እንደኾነ አየ” እያለ አስተሳሰባቸውን ከንቱ ያደርግባቸዋል /አክሲማሮስ ዘቅዱስ ባስልዮስ፣ 2፡2-3/፡፡ እነዚኽ ከሐድያን “እግዚአብሔር ግዙፉን ዓለም አልፈጠረም” ማለት የፈለጉት “አካላዊ ቃል ሰው አልኾነም” ለማለት ነው፡፡ የጥንቶቹ ፈላስፎች በእነ ፕሌቶ ተፅዕኖ እግዚአብሔር ሰው ሊኾን አይችልም የሚሉ ነበርና፡፡ አኹን ደግሞ ከዚኹ በተቃራኒ ነው፡፡ ሎቱ ስብሐትና ኹሉንም ነገር ግዙፍ ሊያደርጉት ይሞክራሉ፡፡ የጌታችንን ልደት፣ ጥምቀት፣ ሞትና ትንሣኤ፣ የመስቀል በዓል ሥጋዊ አስተሳሰብ እየወረረው ነው፡፡ ኹለቱም ምንፍቅና ናቸው፡፡ ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስም ይኽን በማሰብ የሥነ ፍጥረት አንዱ ዓላማ የአካላዊ ቃል ሥጋዌን የሚያስረዳ መኾኑን በግልጽ ይነግረናል /ዮሐ.1፡1-14/፡፡ ቤተ ክርስቲያን ትምህርቷን በሥነ ፍጥረት መዠመሯምና “የማይታይ ታየ፤ ዘመን የማይቈጠርለት 12፣ 30 ተብሎ ተቈጠረለት፤ የማይሞት ሞተ” እያለች ስለ ሥጋዌ ማስተማሯም ስለዚኹ ነው፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር!!!

No comments:

Post a Comment

FeedBurner FeedCount