Showing posts with label ጥያቄና መልስ. Show all posts
Showing posts with label ጥያቄና መልስ. Show all posts

Friday, July 26, 2013

ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጡር ነውን? - ክፍል ፫ -

በገብረ እግዚአብሔር ኪደ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ ሐምሌ ፲፱ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም)፡ ውድ ጠያቂያችን! እንደምን ሰነበቱ? ዳግም እንድንገናኝ፣ መንፈሳዊ ጭውውትም እንድናደርግ የፈቀደልን ለቸርነቱ ስፋት ለፍቅሩም ልኬት የሌለው ደግ ፈጣሪያችን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተመሰገነ ይኹን፤ አሜን፡፡ እነሆ ለዛሬ ደግሞ ብዙ ስስ ልብ ያላቸው ወገኖች (በተለይም የይሖዋ ምሥክሮችና ሙስሊሞች) ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ፍጡር ነው” ለማለት ከሚጠቅስዋቸው ቃላተ መጻሕፍት ቀዳሚውን ይዘን ቀርበናል፡፡ እርሱም “እግዚአብሔር የመንገዱ መጀመሪያ አደረገኝ፥ በቀድሞ ሥራው መጀመሪያ” /ምሳ.፰፡፳፪/ የሚለው ነው፡፡ እንኪያስ እኛም ከአማናዊው መርከብ እንሳፈርና ከሊቃውንቱ ጋር ሆነን የምሥጢሩን ጽዋዕ እንቅዳ፤ በጥርጣሬ ፀሐይ ደርቆ የተጠማው ልቦናችንም ከማየ ሕይወት እናጠጣው፡፡

Tuesday, October 23, 2012

ሞትን መፍራት ማቆም የሚቻለው እንዴት ነው?



በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
 
ጥያቄ፡- እሞታለሁ ብዬ ሳስብ በጣም እጨነቃለሁ፡፡ እናቴ እንደነገረችኝ ከሆነ ሞትን መፍራት የጀመርኩት ገና ከልጅነቴ ጀምሬ ነው፡፡ አሥራ ሁለተኛ ክፍል ሳለሁ በጣም ከምቀርባቸው ጓደኞቼ መካከል ከአንዱ ጋር ተጣላሁና ሳልታረቀው በሳምንቱ ሞተ፡፡ በጊዜው በጣም ጸጸተኝ፡፡ ሞትን ባሰብኩ ቁጥር የሚታየኝ ያ ሳልታረቀው የሞተው ልጅ ነው፡፡ የመፍራቴ መጠንም በእድገቴ ልክ እየጨመረ ነው፡፡ ሌሊት ላይ ባንኜ “አሁን ብሞትስ?” ብዬ እጨነቃለሁ፡፡ ንስሐ ብገባም ፍርሐቱ ሊለቀኝ አልቻለም፡፡ “ሰው ሞተ” ሲባልም በጣም እደነግጣለሁ፡፡ የምደነግጠውና የምፈራው ግን ሰውዬው ስለሞተ ሳይሆን “እኔም እኮ እሞታለሁ” ብዬ ነው፡፡ እባካችሁ በጣም ጨንቆኛልና ሞትን መፍራት ማቆም የሚቻለው እንዴት ነው?
                             እኅታችሁ ኤልሣቤጥ ነኝ ከአ.አ. 

ምላሽ፡-ውድ ጠያቂያችን! የእግዚአብሔር ፍጹም ሰላምታ ባለሽበት ይድረስሽ፡፡ ለጠየቅሽን ጥያቄ የቻልነውን ያህል ለመርዳት መጻሕፍተ ሊቃውንትን አገላብጠን ያገኘነውን መልስ እነሆ ብለናል፡፡ እንደ ጠቋሚ ይረዳሻል ብለንም እናምናለን፡፡ ከቻልሽ አስቀድመሽ በጸሎት ጀምሪና በተመስጦ ሆነሽ አንቢው፡፡ መልካም ንባብ!

Tuesday, September 4, 2012

እግዚአብሔር የተወሰኑ ሰዎችን ለመንግሥቱ ሌሎችን ደግሞ ለገሃነም ወስኗልን?


በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

አንዳንድ ወገኖች የሰው ዕድል ፈንታው ጽዋዕ ተርታው ከጻድቃን ወይም ከኩንኖች መሆን አስቀድሞ በእግዚአብሔር የተወሰነ ነው በማለት ይናገራሉ፡፡ ለዚህ ቅድመ ውሳኔ /Predestination/ ሐሳባቸውም አስረጅ አድርገው የሚያቀርቧቸው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጥቅሶች አሏቸው /ሮሜ.911-21 ኤፌ.14/፡፡ ከዚህም በመነሣት ድኅነት የሚገኘው ከዘመናት በፊትእግዚአብሔር በወሰነው መሠረት እንጂ ሰው በሚፈጽመው ሥራ የማይሰጥ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ እስኪ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን በዚህ ጉዳይ ምን ብላ እንደምታስተምርና የእነዚህ ሰዎች አስተምህሮ የሚያመጣው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ተፋልሶ ምን እንደሆነ እንመልከት!

             1.አስቀድሞ ሁሉን ማወቅ ወይስ አስቀድሞ መወሰን?
 እግዚአብሔር ዓለምን ከመፍጠሩ በፊት እስከ ዓለም ፍጻሜ ሊሆን ያለውን ነገር ምንም ሳይሰወርበት ሁሉን ያውቃል፡፡ አንድ ሰው ከቅዱሳን ወገን አልያም ከኃጥአን ወገን እንደሚሆን አስቀድሞ ያውቃል /ሮሜ.828-30/፡፡ ሆኖም ግን የተወሰኑትን ለመንግሥተ ሰማያት የተወሰኑትን ደግሞ ለገሃነም ለኩነኔ አልፈጠራቸውም፡፡ እንዲህ ቢሆንስ ኖሮ እግዚአብሔር አንድስ እንኳ ይጠፋ ዘንድ እንደማይፈልግ ባለተናገረ ነበር /2ጴጥ.39/ የዓለም ሕዝብ በሙሉ ለድኅነት መጥራት ባላስፈለገ ነበር /ማቴ.2819 ሮሜ.819/ ሰዎች ሁሉ ይድኑ እውነትንም ያውቋት ዘንድ ባልወደደ ነበር /1ጢሞ.24/፡፡ በመሆኑም ሰው ከእግዚአብሔር በተቀበለው ነጻ ፈቃዱ ተጠቅሞ ወይ ርትዕት በሆነች የሕይወት መንገድ ይጓዛል አሊያም የሞት መንገድ በምትሆን በኃጢአት መንገድ ይሄዳል፡፡ ድኅነት ለሁሉም የተሰጠ ቢሆንም የሰው ድኅነቱ በራሱ መሻትና የነጻ ፈቃድ ምርጫ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ሄሬኔዎስ የተባለ አባትም፡- ጥቂቶች በተፈጥሮ ክፉ ቢሆኑ ሌሎችም መልካም ቢሆኑ መልካሞቹ ስለ መልካምነታቸው መልካም ሠሩ ተብለው ምስጋና የተገባቸው አይሆኑም፡፡ ሲፈጠሩ እንዲህ ሆነው ነውና፡፡ ክፉዎቹም ስለ ክፋታቸው ነቀፌታን ባላገኛቸው ነበር፡፡ ጥንቱንም ሲፈጠሩ እንዲህ ሆነዋልና ብሏል /Iraneus, Book IV, Chap.37/፡፡ 

             2. እግዚአብሔር አያዳላም ፍርዱም ርቱዕ ነው!
 እግዚአብሔር የተወሰኑ ሰዎችን ለመንግሥተ ሰማያት ሌሎችን ደግሞ ለገሃነም አስቀድሞ ወስኗል ማለት ክብር ምስጋና ለስም አጠራሩ ይሁንና እግዚአብሔር ያዳላል እንደማለት ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ግን አምላካችሁ እግዚአብሔር የአማልክት አምላክ፣ የጌቶች ጌታ፣ ታላቅ አምላክ፣ ኃያልም፣ የሚያስፈራም፣ በፍርዱም የማያዳላ፣ መማለጃም የማይቀበል ነው /ዘዳ.1017/ እግዚአብሔር ለሰው ፊት እንደማያዳላ በእውነት አየሁ /ሐዋ.1034/ ከእግዚአብሔር ዋጋችሁን እንደምትቀበሉ ታውቃላችሁ፤ ለክርስቶስ ትገዛላችሁና፤ የሚበድል ግን ፍዳውን ያገኛል እርሱም አያደላለትም ይላል /ቈላ.323/፡፡  

           3.አስቀድሞ መወሰን አለ ከተባለ ትእዛዛት ለምን ተሰጡ?
 እግዚአብሔር የተወሰኑትን ሰዎች ለመንግሥተ ሰማያት የተወሰኑትን ደግሞ ለገሃነም ፈጠረ ከተባለ ሰዎች በአእምሮ ጠባይ መሪነት፣ በሥነ ፍጥረት አስተማሪነት፣ በሕገ ልቡና አዋቂነት መልካም ሥራ መሥራት

Tuesday, July 17, 2012

የሃይማኖታችን ሊቀ ካህናት- የመጨረሻው ክፍል (ክፍል አምስት)!


      በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
  ተወዳጆች ሆይ! እንደ እግዚአብሔር ሐሳብ ለመማማር የጀመርነው ርእስ የሚያልቅ ስላልሆነ እናንተ በይበልጥ ከሊቃውንት ከመጻሕፍት እንድታዳብሩት እየጋበዝኩኝ እኛ ዛሬ እንጨርሳለን፡፡ መልካም ንባብ፡፡
1. ደሙ ከሞተ ሥራ ሕሊናን የሚያነጻ ሊቀ ካህናት ነው፡፡ የዘመነ ብሉይ ሊቃነ ካህናት መሥዋዕቶች የጊደሮች፣ የኮርማዎች፣ የፍየሎች የሆነ ደመ እንስሳ ነበር፤ የዘመነ ሐዲስ ግን በደመ ክርስቶስ የተደረገ ነው፡፡ የዘመነ ብሉይ መሥዋዕቶች ያለ ፈቃዳቸው ያለ ውዴታቸው የሚሞቱ እንስሳት ነበሩ፤ የዛሬው ግን ሞት ይሁንብኝ ይደረግብኝ ብሎ ያለ ኃጢአቱ እንደ ኃጢአተኛ ተቈጥሮ በፈቃዱ እስከ ሞት ድረስ የታዘዘ የእግዚአብሔር በግ ነው፡፡ የእነዚያ መሥዋዕት ነውርና ነቀፋ ባለባቸው አገልጋዮች የሚቀርብ ነበር፤ የሐዲስ ኪዳን መሥዋዕት ግን ነውርና ነቀፋ በሌለበት በንጹሑ ኢየሱስ የተከናወነ ነው፡፡ የእነዚያ መሥዋዕት ሞት በሚይዛቸው በእንስሳት ደም የሚከናወን አገልግሎት ነበር፤ የሐዲስ ኪዳኑ መሥዋዕት ግን ትንሣኤና ሕይወት በሆነው በክርስቶስ የተከናወነ አገልግሎት ነው፡፡ የመጀመርያው ኪዳን ለጊዜው የሆነ ንጽሕናን የሚሰጥ ነበር፤ የሊቀ ካህናችን የኢየሱስ ክርስቶስ አገልግሎት ግን ከጊዜና ከቦታ ቀመር ውጪ (Beyond Time) የሆነ ዘለዓለማዊ ንጽሕናን የሚሰጥ አገልግሎት ነው፡፡ የቀደመው ኪዳን በምሳሌና በጥላ በሆነ በደመ እንስሳ የሚከናወን ነበር፤ የዛሬው ግን አማናዊ በሚሆን በንጹሑ በደመ ክርስቶስ ተደርጓል፡፡ የቀደመው መሥዋዕት እሳት አንድዶ እንጨት ማግዶ የሚሠዋ ነበር፤ የዛሬው ግን በመንፈስ ቅዱስ እሳትነት የተደረገ ነው፡፡ እንዲህም ስለ ሆነ የእነዚያ መሥዋዕት ደመ ነፍስን (ሥጋን) ብቻ የሚቀድስ ነበር፤ የዛሬው ግን… ደመ ክርስቶስ ግን ሕያው መሥዋዕት ስለሆነ ሁለንተናን ሕያውና ቅዱስ የሚያደርግ ነው፤ ሕሊናን ከሞተ ሥራ የሚያነጻ ልዩ መሥዋዕት ነው፡፡ ሐዋርያው እንዲህ ይላል፡- “ደመ ላህም ደመ ጠሊ የጊደርም አመድ ሥጋዊ ኃጢአትን የሚያነጻ ከሆነ፣ በኃጢአት ያደፉትን የሚያከብራቸው ከሆነ በመንፈስ ቅዱስ እሳትነት ራሱን ለእግዚአብሔር ነውር ነቀፋ የሌለበት የዘለዓለም መሥዋዕት አድርጎ ያቀረበ የኢየሱስ ክርስቶስ ደምማ ከኦሪት፣ ከኃጢአት፣ ከፍዳ፣ ከፍቅረ ንዋይ ልቡናችንን እንደምን ያህል ያነጻ ይኾን?” /የዕብ.9፡13-14 ትርጓሜው፣ገጽ.441/፡፡  ስለዚህ ደሙ ከሞተ ሥራ ሕሊናን የሚያነጻ ሊቀ ካህናት አለን፡፡
2. የሐዲስ ኪዳን መካከለኛ (ምርጥ) ሊቀ ካህናት ነው፡፡ ሐዋርያው “ስለዚህም የፊተኛው ኪዳን ሲጸና ሕግን የተላለፉትን የሚቤዥ ሞት ስለ ሆነ፥ የተጠሩት የዘላለምን ርስት የተስፋ ቃል እንዲቀበሉ እርሱ የአዲስ ኪዳን መካከለኛ ነው ይላል /ዕብ.9፡15/፡፡ እውነት ነው! ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለወንጌል መምህር ለመንግሥተ ሰማያትም አስታራቂ የሐዲስ ኪዳን ብቸኛው መካከለኛ ነው፡፡ ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ይህን ክፍል በተረጐመበት አንቀጽ ምን ማለት እንደሆነ እንዲህ ያብራራልናል፡- “መካከለኛ ማለት ምን ማለት ነው? መካከለኛ መካከለኛ ለሆነለት ነገር ባለቤት (ተጠቃሚ) አይደለም፡፡ ለምሳሌ አማጭ (መካከለኛ) ለሚያገባ ሰው ሚስት ለማግባት አጋዥ ይሆነዋል እንጂ እርሱ የሚያገባ ሙሽራ አይደለም፡፡ በጌታም ዘንድ እንዲህ ነው (የተሠዋው እጠቀም ብሎ አይደለም)፡፡ ወልድ ዋሕድ ጌታ በአባቱና በእኛ መካከል አስታራቂ ሆነ፡፡ አብ በሠራነው ኃጢአት ፈርዶብን መንግሥቱን ሊያወርሰን አልወደደም ነበርና ተቀዳሚ ተከታይ የሌለው የባሕርይ ልጁ በእርሱና በእኛ መካከል አስታራቂ ሆነ፡፡ እርሱንም ደስ አሰኘው፡፡ ከዚያም እኛን ወደ ልጅነት ልጅነትንም ወደ እኛ ጠራ፤ በሞቱ ከአብ ዘንድ መንግሥተ ሰማያትን አስገኘልን፡፡ ሕጉን በማፍረስ በነበርን ጊዜ ሞት ተገባን፤ እርሱ ግን ስለ እኛ በሞተ ጊዜ ሳይገባን ለመንግሥተ ሰማያት የበቃን አደረገን፡፡ አባት ለልጁ እንደሚሰጥ ቀድሞ ልጅነትን ሳንጥር ሳንግር እንዲያው ሰጠን”  /ድርሳን ዘቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ፣ ድር.16፡33-48/፡፡ አዎ! በበደልነው ጊዜ ሕጉ (ኦሪት) እንደ ፍርድ ሆነብን (የሚያስፈርድብን ሆነ)፡፡ ለማዳን የሚሞት አንድ ስንኳ ጠፋ፡፡ ሊቀ ካህናችን ግን ከባሕርይ አባቱ ከአብ፣ ከራሱና ማኅየዊ ከሚሆን ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ያስታርቀን ዘንድ የባርያውን መልክ ይዞ (የእኛን ባሕርይ ነሥቶ) ትምክህታችን ከምትሆን ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ ሰው ሆነ፤ አምላክ የሆነ ሰው ሰውም የሆነ አምላክ (መካከለኛ) ሆነ፤ በተዋሕዶ አንድ አካል አንድ ባሕርይ የሆነ ሥግው ቃል (Incarnated Word)፣ አምላክ ወሰብእ (መካከለኛ) ሆነ፡፡ አስቀድመን እንደተናገርነው በሥግው ቃልነቱ ስለ እኛ ባይሞት ኖሮ ኦሪት ደካማ ከመሆኗ የተነሣ ባልዳንን ነበር፡፡ ስለዚህ እንደ ሰውነቱ ዘመዳችን እንደ መለኰትነቱ ፈጣርያችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለአዲስ ሕግ ለወንጌል መምህር ለመንግሥተ ሰማይ አስታራቂ ሆነ፤ በሰውና በእግዚአብሔር መካከል ያለ ብቸኛ መካከለኛ ሆነ፡፡
3. ራሱን በመሠዋት ኃጢአትን የሻረ ሊቀ ካህናት ነው፡፡ ደጋግመን እንደተናገርነው የቀደመው ሊቀ ካህናት ብዙ ጊዜ ብዙ መሥዋዕት ሠዋ፤ ሊቀ ካህናችን ግን አንድ ጊዜ ራሱን ሠዋ፡፡ የቀደመው ሊቀ ካህናት ገንዘቡ ባይደለ በሌላ ደም አገለገለ፤ የዛሬው ግን እውነት ገንዘቡ በሚሆን በራሱ ደም አስታረቀ፡፡ ምሥዋዑ እርሱ ነውና፤ የሠዋው እርሱ ነውና፤ የተሠዋውም እርሱ ነውና በራሱ ደም አገለገለ፡፡ ፈቃዱን እንደ ካህን ሥጋው እንደ መንበር አድርጎ ነፍሱን አንድ ጊዜ ሠዋ፡፡ አሁን ግን በዓለም ፍጻሜ (ኑሮ ኑሮ አምስት ሺ አምስት መቶ ዘመን ሲፈጸም) ራሱን በመሠዋት ኃጢአትን ሊሽር (ያጠፋት ዘንድ) አንድ ጊዜ ተገልጦአል” /ዕብ.9፡26/ ተብሎ እንደተጻፈ ሊቀ ካህናችን ኢየሱስ ክርስቶስ የዓለምን ኃጢአት ያስወገደው ራሱን በመሠዋት እንጂ የጊደርና የኮርማ ደም በማፍሰስ አይደለም፡፡
4. ያዳናቸውን ወደ መንግሥተ ሰማያት ለመውሰድ ሁለተኛ የሚገለጥ ሊቀ ካህናት ነው፡፡ ሐዋርያው እንዲህ ይላል፡- “ለሰዎችም አንድ ጊዜ መሞት ከእርሱ በኋላም ፍርድ እንደ ተመደበባቸው፥ እንዲሁ ክርስቶስ ደግሞ፥ የብዙዎችን ኃጢአት ሊሸከም አንድ ጊዜ ከተሰዋ በኋላ፥ ያድናቸው ዘንድ ለሚጠባበቁት ሁለተኛ ጊዜ ያለ ኃጢአት ይታይላቸዋል” /ዕብ.9፡27-28/፡፡ ምን ማለት ነው? ውሎ ውሎ ከቤት ኑሮ ኑሮ ከመሬት እንዲሉ ለሰው ኑሮ ኑሮ ሞት እንዲቆየው ኋላም መቃብር እንዲከተለው ሁላችንም ከፊት የሚጠብቀን አንድ ጊዜ “መሞት” አለ፡፡ ሆኖም ግን ይህ “ሞት” ክርስቲያኖች ለምንሆን ለእኛ ከድካማችን ዕረፍት እንጂ እውነተኛ ሞት አይደለም፤ ሞት የሚሠለጥንብን አይደለም፡፡ ሞትስ ሰው የኃጢአቱን ትብትብ ተሸክሞ ሳለ ሥርየተ ኃጢአትን ሳያገኝ መንግሥተ ሰማያትን ሲያጣ ነውና፡፡ ስለዚህ ከድካም ካረፍን በኋላ የዘለዓለም ሕይወት አለን፡፡ ክርስቶስም የብዙዎችን ሰዎች ኃጢአት ያስተሠርይ ዘንድ ኑሮ ኑሮ አምስት ሺ አምስት ዘመን ሲፈጸም አንድ ጊዜ ራሱን ሠዋ፡፡ አዎ! በአዳም ምክንያት የመጣው ሞት ሁሉን ለማጥፋት መጣ፡፡ ክብር ምስጋና ለስም አጠራሩ ይሁንና ጌታችንም ኃጢአት ሳይኖርበት ስለ እኛ ኃጥእ አሰኘ፡፡ እርሱ ንጹሕ ሲሆን “ከኃጥአን ጋር ተቈጠረ” /ኢሳ.53፡12/፤ የእኛን ኃጢአት የራሱ እንደ ሆነ ቈጥሮ ወደ መስቀል ወጣ /2ቆሮ.5፡21/፡፡ ማመንን ደኅንነትን ለወደዱም አዳናቸው፡፡ “አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው” ብሎ /ሉቃ.23፡34/ ሥርየተ ኃጢአትን ሰጣቸው፤ ይቅር አላቸው፡፡ ከእንግዲህ ወዲህ ግን የሰውን ኃጢአት ለመሸከም ሳይሆን ያዳናቸውን ወደ አዘጋጀላቸው ርስት ወደ ሀገራቸው ለመውሰድ ይመጣል፡፡ የዘይት ማሰሮአቸውን ሞልተው ተስፋ ለሚያደርጉት፣ ለሚጠባበቁት ለሁለተኛ ጊዜ ያለ ኃጢአት ይታይላቸዋል፤ ይመጣላቸዋል፡፡ ዓለምን ለማሳለፍ፣ ጻድቃንን ለማወደስ፣ ኃጥአንን ለመውቀስ፣ ሞትንና ዲያብሎስን ወደ ጥልቁ በመጣል ለመደምሰስ፣ መንግሥቱንም ለምእመናን ለማውረስ ይመጣል፡፡ ወንድሜ!... እኅቴ!... የኢየሱስን መምጣት ትጠባበቃለህን/ ትጠባበቂያለሽን? እንግዲያው ከወንጌላዊው ጋር፡- “ይህን የሚመሰክር አዎን በቶሎ እመጣለሁ ይላል፤ አሜን ጌታ ኢየሱስ ሆይ ና” እንበል /ራዕ.22፡20/፡፡

      ስናጠቃልለው ሰዎች ሁሉ ሊድኑና እውነቱን ወደ ማወቅ እንዲደርሱ የሚወድ ደግሞም  የምናመልከው እግዚአብሔር አንድ ነው፡፡ እንዲያድነንና ወደ እውነት (ወደ ራሱ) ሊመራን ቤዛም ሊሆነን በተለየ አካሉ ትምክሕታችን ከምትሆን ከቅድስት ድንግል ማርያም ፍጹም ሥጋንና ፍጹም ነፍስን ተዋሕዶ የመጣም አንዱ እውነት እግዚአብሔር ወልድ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ እንዲህ ስለሆነም መካከለኛ መባልን ተገባው፡፡ “እግዚአብሔር አባቴ ነው”፤ “በአባቴ ስም መጣሁ”፤ “እኔና አብ አንድ ነን” ብሎ የመሰከረውን ምሥክርነት ያልተቀበሉት ባይቀበሉትም በገዛ ዘመኑ (በመዋዕለ ሥጋዌው) ምስክርነቱ ነበረ /1ጢሞ.2፡4-6/፡፡ እኛም ከቅዱስ ጳውሎስ ጋር ሆነን ይህን እውነት እንናገራለን፤ አንዋሽም፡፡ ብዙዎች ሌላ መካከለኛ እንዳለን አድርገው ቢከሱንም “ከአንዱ ሊቀ ካህናችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ውጪ ሌላ መካከለኛ የለንም” ብለን እንመሰክራለን፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር የታረቅንበት የመንግሥተ ሰማያትን መንገድ በደሙ የመረቀልን ሊቀ ካህናችን አንድ ነው፤ እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ ይባላል ብለን እንመሰክራለን፡፡ የቅዱሳንን ምልጃ ከኢየሱስ ክርስቶስ ሊቀ ካህንነት ጋር ፈጽሞ የማይገናኝ ነውና “ሌላ መካከለኛ” የለንም ብለን እንመሰክራለን፡፡
አኰቴት ወክብር ለሊቀ ካህንነ ለኢየሱስ ክርስቶስ ምስለ አቡሁ ወምስለ መንፈሲሁ እስከ ለዓለም አሜን!! 

FeedBurner FeedCount