Saturday, June 30, 2012

ስምህ


 ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ! መንፈሳዊ ምስጋና ሁሉ ለአንተ ይገባል፡፡ ዋጋው የማይታወቅ ነጋዴ ገንዘቡን ሁሉ ሰጥቶ የተወዳጀው እውነተኛ ዕንቁ ደንጊያ አንተ ነህ፡፡ ይህንን የዕንቁ ደንጊያ በሰውነታችን ውስጥ ያበራ ዘንድ ደግሞ ዛሬ ለእኛ አድርግልን፡፡ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ! የተቀደሰው ስምህ የልባችን ደስታ የሰውነታችን ሽልማት ጌጥ ነው፡፡


 አቤቱ ምድርንና ዓለሙን ሁሉ ዞርሁ ያለ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ስም በቀር ጣፋጭ ስምን አላገኘሁም፡፡ በምድር ላይ የሚደረግ ረድኤትና ኃይል ሁሉ ያለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም በቀር አይሆንም፡፡ እግዚአብሔርን ያገለገሉ የሰው ወገኖች ሁሉ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኵል ነው፡፡ የከበረና የተመረጠውን እጅ መንሻ ሁሉ ያለ ኢየሱስ ክርስቶስ ስም አልተቀበልንም፡፡ ሰማይና ምድር ያለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ከሁከት አልጸኑም፡፡

 የጌታዬ የኢየሱስ ክርስቶስ ስም ከማር ከወለላና ከሦከር ይጥማል፡፡ ማርና ሦከር በሚበሉበት ጊዜ ይጠገባሉ፤ የጌታዬ የኢየሱስ ክርስቶስ ስም ግን አይጠገብም፡፡ የጌታዬ የኢየሱስ ክርስቶስ ስም በምጠራ ጊዜ ከንፈሮቼ ማርን ያንጠባጥባሉ፡፡ ማር፣  ስኳርና እንጀራ ቢሆኑም እንደ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ስም በእኔ ዘንድ ጣዕም የላቸውም፡፡ የጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ይሻለኛልና ከሰማይ በታች ካለ ፍጥረት ሁሉም ይበልጣልና፡፡

 ቸርነትህ ብዙ ነው፤ አይነገርምም፡፡ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ! በሚያምንብህና በሚወድህ አፍ ሁሉ ስምህ የታወቀ ነው፡፡ በሕግ ከታወቁ ምስጋናዎች ሁሉ ከውስጣቸው የሚመስልህ የለም፡፡ የዓይኖቼ ብርሃንና የሥጋዬ ብርታት ከከበረው ስምህ ወገን ነው፡፡ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ! እስከ ሕይወቴ መጨረሻ የከበረ ስምህን በአንደበቴ ዘወትር የተሾመ አድርገው፡፡ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ክርስትያን ሰውነት ሁሉ የጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ  ስም በአንድነት ያከብራሉ፤ ያመሰግናሉ፡፡

 ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ! ከኃጢአት ወገን የሚሆን የክፋት መንፈስን ሁሉ ከእኔ አስወግድ፡፡ መዳኛችን በሚሆን በዚህ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ክርስቲያኖች ሁላችሁም ፈጽሞ ደስ ይበላችሁ፡፡

 የጌታዬ የኢየሱስ ክርስቶስ ስም ጣፋጭ ነው፤ በገነት ካለ ፍሬም ይልቅ ይጣፍጣል፡፡ አባታችን ዳዊት በአመሰገነበት በከበረ መዝሙር የጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስን ስም ፈጽሞ እናመሰግናለን፤ እናከብራለን፡፡

 ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ! ብዙ የሆነ የመንፈስ ቅዱስን ጸጋ በእኔ ላይ አሳድር፡፡ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ! አንተን ደስ የማያሰኝህን ሓሳብ ሁሉ ከእኔ ታርቅ ዘንድ ወዳንተ እለምናለሁ፤ ከአንተም እሻለሁ፡፡ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ! በጌትነትህ ከእኔ ጋር ቸርነትህን አድርግ፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ እንሰግድልሃለን! ፈጣሪያችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ እንሰግድልሃለን! መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ሰማያዊ ከሚሆን ከቸር አባትህ ጋራ ማኅየዊ ከሚሆን ከመንፈስ ቅዱስ ጋር እንሰግድልሃለን፡፡ አሜን!”  የተወደደ ስምዖን ዐምዳዊ
(ምንጭ፡ ግብረ ሕማማት)

No comments:

Post a Comment

FeedBurner FeedCount