በዲ/ን
ስመኘው ጌትዬ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ መጋቢት 1 ቀን፣
2006 ዓ.ም.)፡- በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሃዱ አምላክ
ጸልዩ እምቅድመ
ንባበ ዝንቱ ክርታስ
ለመወለዱ ጥንት በሌለው፣
አስቀድሞ አለም ሳይፈጠር በመለኮቱ ከአብ በተወለደ፣
ዳግመኛም እኛን ለማዳን በዘመኑ እኩሌታ ከቅድስት ድንግል ማርያም በተወለደ በአንዱ የእግዚአብሔር ልጅ ስም
እንደ ሐዋርያት ባለ ሰላምታ ሰላም ለእናንተ
ይሁን፡፡ ዛሬም እንደሌሎች የፆም ቀን
ለቤቱ ምስጋናን በከሚያቀርበው ኢትዮጵያዊ ሊቅ ጋር ጥቂት
ቃላትን መርጠን በነፍስ ዜማ እንቆያለን፡፡
“ተክዕወ በላዕሌየ ትዕዛዘ ኦሪት ወነቢያት
. . . የኦሪትና የነቢያት ትዕዛዝ በላዬ ላይ ፈሰስ፤
አቤቱ ሕግህ ለእግሬ መብራት ለመንገዴ ብርሃን ነው፡፡ ዳግመኛም ሕግህ የጽድቅ
ቃላትን ማወቅ ነው፡፡ ፍፁም መዋደድ
ከሞት ታድናለች፡፡” ጾምን እንፁም፤ እግዚአብሔርን እናምልክ፤ ትዕዛዙን እንጠብቅ፤ በመንገዱ በእርሱ ብርሃንነት እንመላለስ የሚሉት ህጎች ሁሉ
ሰውነቴን የሚያረሰርሱኝ ዝናሞች በእኔ ላይ የፈሰሱ
ጊዜ ለምስጋና እተጋለሁ፡፡
“እገይስ ሐቤከ እቀውም
ቅድሜከ . . . ወደ አንተ እገሰግሳለሁ፡፡ በፊትህ
እቆማለሁ፡፡ ነገርህ ለጉሮሮዬ ጣፋጭ ነው፡፡ በጠዋት ፀሎቴ በፊትህ
ትድረስ፡፡ ፈቃድህን እንድፈጽም አነሳሳኝ (አድርገኝ)፡፡” ዛሬም ማልዶ ወደ
ቤተክርስቲያን በምስጋናው መንበር ፊት ለፀሎት እቆማለሁ ይለናል፡፡ እናንተም እንዲሁ ለስጋችሁ ስንፍናን አታሳዩት፡፡
ታላላቅ ብርሃናትን በሰማይ ያደረግህ፤ ልንመረምራቸው የማንችላቸውን ፍጥረታት በየብስና በባህር ያከናወንክ፤ ጨለማን አሳልፈህ ብርሀንን የምትሰጥ፤ በአንተ ህግ ዓለም
የፀና፤ አቤቱ አንተን አመስግነን የማንጨርስህ በፊትህ እንቆም ዘንድ ፍቀድልን፡፡
እኛ ህዝበ ክርስቲያን ሁላችን በቤትህ እናመሰግንሀለን፡፡
“እንተ የዐውድዋ
ህዝብ ብዙኃን ህንፃሀ. . . ብዙ ህዝብ የሚከቧት፣
በሰማይ አምሳል የተሰራች፣ ህንፃዋ ያማረ ነው፡፡ ወደ እርሷ
እንገስግስ፡፡ ለምህረት አምላክ ምስጋና እናቅርብ፡፡” አቤቱ ቤትህ ልዩ
ናት፡፡ በፆም ጊዜ ከእርሷ
እንጠለላለን፡፡ የዓለምን የጎርፍ ፈሳሽ የመዓበሉን ኃይል በእርሷ
ውስጥ ሆነን እናልፋለን፡፡ ነፋሳት የሚያመጡትን ጥፋት ፈተና
ሁሉ በቤትህ በአንተ ድል እናደርገዋለን፡፡
“ሐነጽዋ ለቤተክርስቲያን ወሣረርዋ በመንፈስ ቅዱስ. . . ቤተክርስቲያንን አነጿት፡፡
በመንፈስ ቅዱስም መሠረቷት፡፡ በሰማያት ምሳሌ ትሆን ዘንድ፣
ከእሳት ነበልባል ታድን ዘንድ፣ የእውነት ደስታን ትሰጠን ዘንድ፣ ሁሉን የሚችል
የማይሳነው ሰላምን በሰላም ላይ ጨምሮ ይስጠን፡፡
“ፆም ትፌውስ ቁስለ ነፍስ
ወታፀምም ኩሉ ፍትወታተ ዘሥጋ . . . ፆም
የነፍስን ቁስል ትፈውሳለች፡፡ የስጋ ፈቃድን
ሁሉ ታስተዋለች፡፡ መልካምነትን ለወጣቶች ታስተምራለች፡፡ ሙሴ በደብረ ሲና ፆሟልና፡፡”
ነፍስ በሀጢአት በበደል ሁሉ ከተወጋች ቁስለኛ መባሏ አይቀርም፡፡
ስለዚህ ይህችን ቁስለኛ ሀኪም ሆኖ የሚፈውሳት
የፆም ባለቤት በፆም ነው፡፡ አልገታ ያለ የጎልማሳነት
ምኞት በፆም ይገታል፡፡ በዚህም የመልካም ሥራ ልምምድ
ሰው ወደ ላይ ያድጋል፡፡
“እግዚእ እግዚአብሔር አሀዜ ኩሉ
ዓለም. . . ዓለምን ሁሉ የያዘ እግዚአብሔር
ጌታ በመስቀሉ የሚረዳ የሚያድን ነው፡፡ በውኑ በእግዚአብሔር አምኖ የጠፋ
አለን? የደረቀ እንጨት እንኳን ተቆርጦ ዳግመኛ ያፈራል፤ ተስፋም አለው፡፡” አቤቱ ሰውን ማመን
ከንቱ ነው፡፡ በሀያላንም ተስፋ ማድረግ አይጠቅምም፡፡ በፆማችን አንተ ብቻ
ተስፋችን ነህ፡፡ እንደ ተቆረጠ እንጨት ብንደርቅ እንኳን ልታለመልመን የታመንክ ነህ፡፡
“ ናሁ ትዕዛዘ
ሀዲሰ እፅህፍ ለክሙ. . . አሁን አዲስ
ትዕዛዝን እፅፍላችኋለሁ፡፡ እርስ በእርሳችሁ ተዋደዱ፡፡ ዘወትር በመካከላችሁ ሰላም ይሁን፡፡
ጠላታችሁን ውደዱ፡፡ በእናንተ ሊደረግባችሁ የማትፈልጉትን በሰው አታድርጉ፡፡”
አሁን ልንለያይ
ነው፡፡ ግን እኔ ሳልሆን
ቅዱስ ያሬድ መርቆን በዜማ ነግሮን
እንለያይ፡፡ “ሰላመከ እግዚኦ ሐበነ ዘንተ እንዘ
ንገብር. . . አቤቱ ሰላምህን ስጠን፡፡ የቅዱሳንን ሥራ ይህንን
እየሰራን በበጎ ምግባር ሁሉ ወንድማችንን
እንውደድ፡፡” አሜን!
ለእርሱ ልጅነት የማልበቃ ደካማ ስሆን
የማይገባኝን ነገር ስለፃፍኩ ስለእኔ ፀልዩልኝ አሜን በጾሙ
ሰላምን ይስጠን ጾሙን በሰላም ያስፈጽመን አምላከ ቅዱስ ያሬድ
ይጠብቀን፡፡
No comments:
Post a Comment