Wednesday, March 26, 2014

ደብረዘይት ዘሐሙስ



በዲ/ን ስመኘው ጌትዬ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ መጋቢት 17 ቀን፣ 2006 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!

 ጥንት በሌለው፣ ለፊተኛው ፍጻሜ በሌለው፣ አስቀድሞ በነበረ፣ አሳልፎም በሚኖር የእርሱን እስትንፋስ እፍ ብሎ ሕይወት በሰጠን፣ የእርሱን ደም አፍስሶ ዳግም ሰው ባደረገን በልዑል እግዚአብሔር ወልድ ስም ሰላም ይሁንላችሁ::


  አኃውየ ኢታዕብዩ ልበክሙ ወአትሕቱ ርዕሰክሙወንድሞች ሆይ ልባችሁን አታኩሩ፤ ራሳችሁን ዝቅ አድርጉ፤ ነፍሳችሁን ሊረዳት ወደሚችል ወደ እግዚአብሔር እጅ ስር ራሳችሁን ዝቅ አድርጉ፡፡ ወንድሞቼ ሆይ ልባችሁን በወንድማችሁ ላይ አታኩሩ፤ ሁሉም የራሱን ሸክም ይሸከማልና::” የቤተክርስቲያን ልጆች ሆይ! በጠዋት በቤቱ በጸሎት የጀመራችሁትን ውሎ በትሕትና ጨርሱት:: የቀደመው ፍጥረት በትዕቢት እንደወደቀ ተማሩ:: እናንተ ግን የተስፋችሁን መሠረት ክርስቶስን ያዙ፤ እርሱ ያበራላችኋል ይለናል ዜመኛው::

 ፀወንነ ወኃይልነ ክርስቶስ ብነ ሊቀ ካሕናትመጠጊያችን፣ ኃይላችን፣ ሊቀ ካሕናት ክርስቶስ አለ:: ካሕናቶችህ ጽድቅን ይለብሳሉ፤ ቅዱሳኖችህም ይደሰታሉ፤ ወደ ሕይወትም ይሄዳሉ፤ ሕግ እና ሥርዓት አላቸው፤ መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናት፤ መንግሥተ ወንጌልን ነገሩ፤ ጽድቅን ሰሩ፤ ተስፋቸውንም አገኙ::” ካሕን ተብሎ ካሕናት አስባለን:: ንጽሕናውን ግን ገንዘብ ማድረግ አቅቶን በትንሽነት መኖርን መረጥን:: የሚጠፋ እና የሚያታልል ብል ነቀዝ የሚያበላሸውን ተመኘን:: የመንግሥቱን ነገር ቸል ብለን ስለራሳችን ምድራዊ ሕይወት እንኳን ጊዜ አጣን:: ተስፋ ያስደረግኸንን የገነት ምንጭ ማየት ተሳነን:: የመስቀሉን ትምክሕት ከእኛ አራቅን:: “እንመለስ፤ እንጹም፤” እያለ ዜመኛው ይጠራናል::

 ሰማዕታቱሁሰ ለክርስቶስ አምጣነ ተሰዱየክርስቶስ ምስክሮቹ በዚህ ዓለም ቢሰደዱ በሚመጣው ዓለም ፈጽሞ ይደሰታሉ::” ለእርሱ ምስክርነታችን አሁን በደም አይደለም፤ በእሳትም አይደለም፤ በመታረድ በመሰቀልም አይደለም፤ ነገር ግን ትዕዛዙን በመፈጸም እና በፍቅር እርሱን በመምሰል ነው እንጂ::

 እንዘ ይጔጉዑ ከመ ይርአዩፊታቸውን ለማየት እየቸኮሉ በሕይወታቸው ዘመን ለእርሱ የተገዙለት ጻድቃን በብዙ ሰላም ይደሰታሉ፤ ክብር ይገባቸዋል::” በሕይወቱ (በሥጋ ቆይታው) እርሱነቱን ትቶ፣ ስሜቱን ተቆጣጥሮ፣ ደረስኩ ለሚለው ኃጢአት ሳይበገር፣ መገዛቱን ለአምላኩ ብቻ ያደረገ ክብሩ ከፍ ያለ ነው፤ የሕይወቱ ሰላምም ወደር የለውም::

  ጽድቀ ተመሀሩ ለነዳያን ግበሩ ምሕረተእውነትን ተማሩ፤ ለነዳያንና ለምስኪናን ምሕረትን አድርጉ፡፡ በልዑል ዘንድ ለታመኑ ምጽዋት ከሞት ታድናለች:: ብዙ ከሚቀበል ጥቂት የሚሰጥ ልቡ ሐሴት አለው:: የነፍስና የሥጋ እርካታ የዓለም ምሉዕነት መገለጫ ነው::

ሰላመከ እግዚኦ ሀበነአቤቱ ሰላምህን ስጠን፤ አትጣለንም፡፡ ደስታችንን ወደ ሀዘን አትለውጥ፤ በሕይወታችን ዘመን ሁሉ አንተን እናመሰግንሃለን፤ ተስፋ ለሚያደርጉህ ተስፋቸውን አታጥፋ፤ ሥራህን አስብ::” አሜን!

No comments:

Post a Comment

FeedBurner FeedCount