Thursday, March 13, 2014

ምኩራብ ዘዓርብ



በዲ/ን ስመኘው ጌትዬ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ መጋቢት 4 ቀን 2006 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

 እስከሞት ድረስ በወደደን፣ ስለፍቅር በሞተልን፣ በዚያች ቀን በቀኙ ባለው በኩል፣ ዛሬ ከእኔ ጋር ናችሁ ባለን፣ የእርሱን የምሕረት ቃል ከመስማት የበለጠ ደስታ በሌለን፣ በ30 ዘመን ፍቅሩ የሺህ ዘመን ኃጢአታችንን በደመሰሰልን፣ የምሕረቱን ጥልቅነት በሰውኛ ቋንቋችን ልንገጸው በማንችለው፣ በመስቀሉ ደም ቤዛችን ነፃነትና ሰላምን ባጎናጸፈን ሰላም ለእናንተ ይሁን!!


 “ወሪድየ ብሔረ ሮሜ ለቤተክርስቲያን ርኢክዋ አዕመርክዋ አፍቀርክዋ… ሮሜ ሀገር ሄጄ ቤተክርስቲያንን አየኋት፤ አወቅኋት፤ ወደድኳት፡፡ እህቴ እንደሆነች ለረጅም ዘመን በጎ አገር አሰብኩ፡፡ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ዳግመኛ አየኋት፡፡ በጢግሮስ ወንዝ ትታጠባለች” በማለት የዕለቱን ዜማ ይጀምራል፡፡ ቤተክርስቲያንን ሮሜ ሄጄ አየኋት፤ ስላአየኋት ፍቅሯ ሳበኝ፡፡ አሁን እርሷን እንደ እህቴ አልለያትም፡፡ እርሷን ያነፃትንም ጌታ እንዲሁ፡፡

 “ገብረ ብረሃናተ ዐበይተ ባሕቲቱ . . . ብቻውን ታላላቅ ብርሃናትን ፈጠረ (አደረገ)፡፡ በፀሐይ ቀንን አስገዛው፡፡ ምሕረቱ ለዘለዓለም ነውና፡፡ በሁሉ ዘንድ ንጉሥ ነው፡፡ ይቅር ባይ እግዚአብሔር ይለምኑ ዘንድ ይወዳል፡፡” የሚለምኑትን የሚሰጥ፣ ብርሃናትን በሕይወታችን ያደረገ፣ እንደ ፀሐይ በርቶ ለትንሿ ጽድቃችን ድምቀትን የሰጠ፣ ዛሬ እናመሰግንሃለን፡፡ እንደ መቋሚያዎቹ ግራ ቀኝ እያልን፣ እንደ ካህናቱ ያለ እንቅልፍ በመሆን፣ ሌሊቱን ሁሉ ከእርሱ ምህረትን እንለምናለን፡፡

 “ብርሃን አንተ እግዚኦ ዘኢትጸልም ዘበለሥላሴከ አመድካ . . . አንተ የማትጨልም ብርሃን ነህ፡፡ በሦስትነትህ ምድርን ለካሃት፡፡ የነገሥታት ንጉሥ አሸናፊ ቀላዮችን የዘረጋህ የሚያስፈራውንም የወሰንህ ይኸውም በተመሰገነው ስምህ ነው፡፡” ነገሥታትን አትመስላቸውም፤ አንተ ብቻህን የነገስታቱ ንጉሥ ነህና፡፡ አስፈሪውን ሁሉ በስምህ እናሸንፋለን፡፡ ስምህን ስንጠራ የተናዳፊዎች መርዝ- ውሃ፣ የጠላት ጦር- ዕውር የእኛ ፊት- ብሩህ ይሆናል፡፡ እንደ አባታችን ሙሴ በሰጠኸን በትር ሁሉን እናሸንፋለን፡፡ ይኸውም “ነሲዕየ ማዕተበ ዘወልደ እግዚአብሔር . . . የእግዚአብሔርን ልጅ ምልክት ይዤ በሥላሴ ስም አማትባለሁ፡፡ ብወድቅም በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ አማትቤ እነሳለሁ፡፡ በመስቀሉ ሃይል እመካለሁ፡፡ በላይዋ ላይ መስቀል ከበታቿም የመስዋዕቱ መንበረ ታቦት ያለባት ቤተክርስቲያን ምንኛ ያማረች ናት?!

 “መፍቀሪተ ገዳም ሥነ ሕንፃሃ . . . ድኀነትን የምትወድ፣ ሕንፃዋ ያማረ፣ በሮቿ በሥላሴ ስም የታተመ፣ በመለኮት ጨው ምግቧ የጣፈጠ፣ ሰፊ አደባባይዋም ምሕረት የሞላበት ነው፡፡” ምንኛ በጸጋ ላይ ጸጋ ያለባት ቤት ናት፡፡ ጉልላት መስቀል የሐዲስ ኪዳን፡ መስዋዕት በታች ታቦት መሠዊያ፡፡

 በዚህች እመቤት ፊት “በጽባሕ ትብጻሕ ጸሎትየ ቅድሜከ . . .  በጠዋት ጸሎቴ ወደ አንተ ትድረስ፡፡ አምላኬ ወደ አንተ እገሠግሳለሁ፡፡ በምሕረትህ አስበኝ፡፡ የልመናዬን ድምጽ አቤቱ ስማ፡፡ የባሪያህን ጩኸት አትናቅ፡፡ ነፍሴ ለዘለዓለም ታመሰግንሃለች፡፡”

  ከተለመደው የጾም ነገራችንም እንዳንወጣ “በገቢረ ምሕረት ቀድሱ ጾመ . . . ምሕረትን በማድረግ ጾምን ቀድሱ፡፡ ከልቡናችሁ ቂምን አስወግዱ፡፡ አስቀድማችሁ የእርሱን መንግስት ሹ፡፡ ለምሥጋና የተሠራ ልብሱን ትለብሱ ዘንድ” እያለ ያስታውሰናል፡፡

 “እናንተስ” ይላል በሚመስጥ፣ ይህንን አለም ለቀን ወደ አርያም በሚወስደን ዜማ! “እናንተስ ስትጾሙ ራሳችሁን መርምሩ፡፡ ከበሮ እንዲመታላችሁ መለከት እንዲነፍላችሁ በአደባባይ ራሳችሁን አትግለጡ፡፡ አብዝታችሁ አባታችሁ በሚያውቀው ብቻ ጹሙ፡፡ እርስ በእርሳችሁ ተፋቀሩ የጾም አላማው የክርስትናም ግቡ ይህ ነውና፡፡ እንዳይፈረድባችሁ አትፍረዱ፡፡ ማንም ከወገኑ ጋር በቁጣና በሃሜት አይኑር፡፡ ጽድቁን ሰላሙን ፈልጉ፡፡ ከምሥጋናም ፈጽሞ ራሳችሁን አትለዩ፡፡

 በመጨረሻም በዛሬዋ ዕለት ጌታ ተሠቅሎ አዳነን “ከመ ኪያነ ያድኅነነ እሞት ስፍሐ እዳዊሁ ቅዱሳተ ዲበ ዕፀ መስቀል… እኛን ከሞት ያድነን ዘንድ ቅዱሳት የሆኑ እጆቹን በእንጨት መስቀል ዘረጋ፡፡… ከመ ይትሐፈር ጸላኢ ወይኅጣዕ ዘይነበብ ቃለ ኀሡ በላዕሌነ በመስቀሉ ቤዘወነ ትዕምርተ ሰላምነ አልቦቱ ዘይክል አኅድጎተነ ፍቅሮ ለክርስቶስ… ጠላት እንዲያፍር በእኛ ላይ ክፉ ነገር የሚናጋረው እንዲያጣ በመስቀሉ ዋጀን፡፡ መስቀል የሰላም ምልከታችን ነው፡፡ ከክርስቶስ ፍቅር የሚለየን የለም፡፡” የመስቀሉን ፍቅር ያሳድርብን አሜን፡፡  

ለእርሱ ልጅነት የማልበቃ ደካማ ስሆን የማይገባኝን ነገር ስለፃፍኩ ስለእኔ ፀልዩልኝ አሜን፡፡ በጾሙ ሰላምን ይስጠን ጾሙን በሰላም ያስፈጽመን፡፡ አምላከ ቅዱስ ያሬድ ይጠብቀን፡፡

No comments:

Post a Comment

FeedBurner FeedCount