Saturday, March 8, 2014

ምኩራብ ዘሰንበተ ክርስቲያን



በዲ/ን ስመኘው ጌትዬ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ የካቲት 29 ቀን 2006 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሃዱ አምላክ

ጸልዩ እምቅድመ ንባበ ዝንቱ ክርታስ

 በነጻነት ልንኖር ክርስቶስ ነጻነት አወጣን፤ እንግዲህ ጸንታችሁ ቁሙ እንደ ገናም በባርነት ቀንበር አትያዙ።”(ገላ 51) በዚህች የክርስቲያን ሰንበት በተባለች ቀን ለሰው ልጆች ሲል በአይሁድ ምኩራብ ለታሰሩት መፈታትን፣ ለባሮች ነጻነትን፣ ለድሆች ፍርድን ሰበከ፡፡ በሚያስደንቅ ትምህርቱ አይሁድ እንኩዋን እስኪደነቁ ድረስ ሰንበታቸውን የጉልበት ሳትሆን የፍቅር፣ ለእነሱ እንጂ እነሱ ለእሷ እንዳልተፈጠሩ አስተማራቸው፡፡ እንግዲህ ይህ ሰላም የተነገረባት የጌታ ቀን በተባለች በዛሬዋ እለት ሰላም ለእናንተ ይሁን፡፡

 የዐቢይ ጾምን ከጀመርን እነሆ ሦስተኛ ሳምንታችን፡፡ ይህ ሳምንት ምኩራብ ይባላል፡፡ ጌታ በአይሁድ ምኩራብ ገብቶ ስለማስተማሩ ሊቁ ቅዱስ ያሬድ ድርሰቱን ዛሬ ስለጀመረበት እና ድርሰቱ አብዛኛውን ስለዚህ ጉዳይ ስለሚናገር ስሙን አግኝቷል፡፡ ከብሉይ እና ከሐዲስ ጠቅሶ የሰንበትን ክብሯን እና የሚተገበርባትንም መልካም ግብር ጌታም በዚህች ዕለት ያደረገውን ተአምር ድውያንን መፈወሱን ጨምሮ በዋነኛነትም በምኩራብ በሐይልና በስልጣን ማስተማሩን በዜማ ከኪሩቤልና ከሱራፌል ጋር ተደምረን እንድናዜም ይጋብዘናል፡፡

 በዕለተ ሰንበት ቦአ ኢየሱስ ምኩራበ አይሁድ …. በሰንበት ቀን ኢየሱስ ወደ አይሁድ ምኩራብ ገባ፤ አስተማራቸው፤ እንዲህም አላቸው እኔን ባታምኑ ስራዬን እመኑ ለረጅም ዘመን እለታትን ሰንበቶችንም እንጃ አልለያችሁምየሃይማኖት ቃልንም አስተማረ ከመስዋዕት ይልቅ ምጽዋትን እወዳለሁትምህርቱን የቃሉን ውበት አደነቁቤተሰብ ገዢ ሁሉ ይረፍባትአይሁድን እንዲህ አላቸው የአባቴን ቤት እንግዲህ መሸጫ መለወጫ አታድርጉት፡፡ የአባቴ ቤት የጸሎት ቤት ነው፡፡ የሰንበት ጌታዋ የምሕረትም አባቷ እኔ ነኝ፡፡ ሕይወትን ታገኙ ዘንድ ሰንበትን አክብሩመላእክት በሰማያት ጻድቃን በገነት ሰንበትን ያከብሯታል፤ ባሕር ታከብራለች፡፡ ፍጥረት ሁሉ ዓሳዎች እና አንበሬዎች በመቃብር ያሉ ያከበሯታል፡፡ እርሱ ከስራው ሁሉ አርፎባታልናኢየሱስ አይሁድን የሰንበት ጌታዋ እኔ ነኝ አላቸው ቤቴን ገበያ አታድርጉት ቤቴ የጸሎት ቤት ይባላልና፡፡እንግዲህ ከምርኮ ለተመለሱ አይሁድ ቃሉን በሚሰሙበት ምኩራብ ሕግ ይጣስባት በነበረችው ሰንበት ሕግን ሊያከብር ሊያስከብር የስጋ ነገር ነግሶባት በነበረችው ምኩራብ ቤቱን ሊያጸዳ ሁለቱን ሰንበትንና ምኩራብን እንደ አይሁድ ሳይሆን እንደ ሐዲስ ኪዳን ስርዓት ሊፈጽማቸው ገባ፡፡ የሐይማኖትን ቃል ምስራችንም እስከዛሬ ነቢያት ያኔም በመምህራነ አይሁድ ባልሆነ ሥርዓት ያውም እንደ ነቢያትይቤ እግዚአብሔር - እግዚአብሔር ይላል” ሳይል እንደ አይሁድምየሙሴ ሕግ” ሳይል በሚደነቅ ትምህርት በግርማአንሰ እብል- እኔ እላችኋለሁ” እያለ በጥበብና በኃይል አሰተማራቸው፡፡

 ከመስዋእት ይልቅ ምጽዋትን እወዳለሁ፡፡ መስዋዕት ለልማድ ምጽዋት ግን ከልብ ናቸውና፡፡ ሰንበትን ስለእናንተ ጌታዋ ሆኜ ጌታዋ ትሆኑ ዘንድ ፈተጠርኩላችሁ እንጂ እናንተ ስለሰንበት አልተፈጠራችሁም ስለዚህ ስንበትን አክብሩ እንጂ ለሰንበት አትገዙ በሰንበት ከኀጢአት ስራ ሁሉ እረፉ፡፡ በላይ በሰማይ በታች በምድር በሙታን ዘንድ በእንስሳት ሳይቀር ይከበራልና በሰንበት ከቤቴ አትለዩ፡፡ ቤቴ የእኔ የአባቴ ነው፡፡ አባቴ ለቅድስና ሰጣችሁ እንጂ ህዝቤ ላይ ቀንበር አጽንታችሁ ትገዙበት ዘንድ የወንበዴም ዋሻ ታደርጉት ዘንድ አልሰራላችሁም ፡፡ ስለዚህ ባለቤቱን ካልናቁ አጥሩን አይነቀንቁ ነውና እኔንና አባቴን ብታከብሩ ቤቴን የወንበዴዎች፣ የኪስ አውላቂዎች፣ የጉቦኞች፣ የንግድ ቤት፣ የመበለቲቱን ሳንቲም ለኪሳችሁ የምትሰበስቡ፣ የህዝብን እንባ ለቤታቸሁ ጡብ የምታቦኩበት ባላደረጋችሁት፡፡ የመጣሁት በስሜ ቀድሼ በደሜ ላጸናት ነው፡፡ ይህን የድኅነት ስራ ከጠላት ከሆነ ከዲያብሎስ ወይም ከእርሱ ካልሆነ በቀር ማንም አይቃወምም፡፡ ቢቃወም ግን በዚያው መጠን በእጄ ጅራፍ ይዣለሁ፡፡ ሻጩንና ለዋጩን በጊዜዬ ከቤቴ አስወጣለሁ፡፡

 በሰንበት ዐርገ ሐመረበሰንበት ወደ መርከብ ወጣ፤ ባሕርን ገሰጸ ኢየሱስ አይሁድንም ገሰጸ ነፋሳትን ገሰጸ ባሕርንም ከወሰኗ እንዳታልፍ ገሰጻትየመርከቡ ሰንሰለቶች እንዳልተበጠሱ ባዩ ጊዜ ቀዛፊዎቹ ተደሰቱ፤ የምስጋና ንጉስን አመስግኑት፡፡ልበ ደንዳኖች አይሁድ ከባህር እንኳን ቀለሉ፡፡ ባህር እርሱን ሰማች እነሱ ግን አልሰሙም፡፡ ይህ ባህር የሚታዘዝለት ነፋሳት ድምጹን የሚሰሙት ማነው እስኪሉ ድረስ የተደነቁበትን አምላክ እርሱም ሊቁ በሚያስደንቅ የነፍስ ዜማ በዛሬዋ እለት አብዝቶ ያመሰግናል፡፡ ለምሰጋና ንጉስ መልኩ ብዙ በሆነ የምስጋና ቅኔ ያዜማል፡፡ እኔ የተመረጡ የአባቴን የዜማ ቃላት ኃይል በሌለው ብዕር ቃላቱን ደርድሬያለሁ፡፡ የቅዱስ ያሬድ አምላክ ሁሉን የሚያውቅ ለነፍሳችን ያንን የሚጥም ዜማ ያሰማት፡፡

 ቅዱሱ የእግዚአብሔር ሰው በፈጸመበት ቃል እሰናበታለሁ፡፡ሰራዕከ ለዕረፍት ወሀብከ በኂሩትከ ሰላመ ለነ ጸጎነ መዝገብከ ዘኢይቀብል በረከትከ ነአኩተከ ወንሴብሐከ ዘአድኀንኮ ለኖኅ አመ አይኅ ወእማይ ብዙኅ እስመ ዘእንበሌከ ባዕድ አምላክ አልቦ ዘነአምር ሰላመከ ሀበነ -- ሰንበትን ሰራህ፤ ለእረፍት ሰጠህ፤ በቸርነትህ ሰላምን ለእኛ ሰጠህ፤ በረከት የማይጎድልበት መዝገብ (ሃብት) በአንተ ዘንድ አለህ፡፡ ኖኅን ከጥፋት ውሃ ያዳንከው እናመሰግንሃለን፡፡ ከአንተ ሌላ እንግዳ አምላክ አናውቅምና ሰላምህን ስጠንአሜን!

ለእርሱ ልጅነት የማልበቃ ደካማ ስሆን የማይገባኝን ነገር ስለፃፍኩ ስለእኔ ፀልዩልኝ አሜን በጾሙ ሰላምን ይስጠን ጾሙን በሰላም ያስፈጽመን አምላከ ቅዱስ ያሬድ ይጠብቀን፡፡

3 comments:

FeedBurner FeedCount