Sunday, March 9, 2014

ምኩራብ ዘሰኑይ



በዲ/ን ስመኘው ጌትዬ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ የካቲት 30 ቀን፣ 2006 ዓ.ም.)፡- በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሃዱ አምላክ
ጸልዩ እምቅድመ ንባበ ዝንቱ ክርታስ
የከይሲን ምክር አጥፍተህ፣ መርዙንም ነቅለህ፣ አስቀድሞ አጥተነው የነበረውን ልጅነታችንን እና መኖሪያችንን በደምህ ንጽሕት ባደረካት ቤተክርስቲያን ተክተህ የሰጠኸን፣ የምኩራብን መስዋእት ሽረህ አማናዊው መስዋእት የሆንከን፣ የድኅነታችን ወደብ በሆንከው በአንተ ሠላማችን ይብዛ፡፡ ሰላም ለሁላችሁ ይሁን!!!
በዚህች የሳምንቱ መጀመሪያ የሥራ ቀን ከእረፍታችን ስንፍና በጠዋት ተነስተን ከቅዱስ ያሬድ ጋር ምስጋናችንን በተመረጡ ጥቂት ቃላት እንጀምራለን፡፡


 ክርስቶስ ብነ ፀወንነ ሀይልነ ፅንዕነ ቤዛነ መድኃኒተ ነፍስነ . . . ክርስቶስ መጠጊያችን፣ ኃይላችን፣ ፅናታችን፣ አዳኛችን የነፍሳችን መድኃኒት ነው፡፡ ከእንቅልፍ ነቃን እርሱንም እናመስግን፡፡ሌሊቱን እኛነታችንን በማናውቅበት የእንቅልፍ ጊዜ ጠብቆ ያሳደረንን፣ ጠዋትም በሰላም ያነቃን ክርስቶስ ነው፡፡ ሐዋርያት ከአንተ ወዴት እንሄዳለን እንዳሉት ከእርሱ ሌላ ምንም የሌለን እኛ ስለሚጠፋው ዓለም ትተን ስለሚመጣው ሕይወት እርሱን ዕለት ዕለት በኑሮአችን ሁሉ እናመስግን፡፡

 እንዲህ ካዜመ በኋላ እንደተለመደው ወደ ቤተክርስቲያን በጠዋት ይሄዳል፡፡ እንዲሁም ይሳለማታል፡-አንቀጸ መድኃኒት ቅድስት ቤተክርስቲያን እምነ ይእቲ ንበላ በሀ. . . የድኅነት በር እናታችን ቤተክርስቲያንን ሰላም እንበላት፤ መሪ ትሆነን ዘንድ፡፡

 ከዚያ ወደ ውስጥ ይዘልቅና የበጎ በጎ ምስጋናውን በመቋሚያ ታግዞ ያለ ድካም ይቀጥላል፡፡እግዚአብሔር የሀበነ ልሳነ ጥበብ ከመ አዕምር ዘዕነበብ. . . የምናገረውን አውቅ ዘንድ የጥበብ አንደበትን እግዚአብሔር ይስጠኝ፡፡ አቤቱ ቃሌን አድምጥ፤ የቤተክርስቲያንን ሕጓን አውቅ ዘንድ ግለጽልኝ፡፡ ወደ እርሷ የመጣ ዋጋውን አያጣም፤ እንግዳ ወዳጅ ናትና፡፡ሰው የሚሰራውን የሚናገረውን ህግን ያውቅ ዘንድ ከሊቁ ጋር፣ ከመዝሙረኛው ጋር፣ ጥበብ እና ኃይልን ልብንና ልቡናን አድለኝ ይበል፡፡ ያለ እውቀት ህዝብ እንደ ከንቱ ነገር ይጠፋልና፡፡ ባለማወቅ ንግግር ነፍስን እናጠፋ ይሆናል፡፡ ህግን ባለመጠንቀቅ ከመንገድ እንስት ይሆናል፡፡ አቤቱ ጥበብን ስጠን፡፡

 የእግዚአብሔር ሀገር፣ የአዲስ ኪዳን ፅዮን፣ ቤተክርስቲያንን አሁንም ሊቁ ያወድሳታል፡-ሀገረ ክርስቶስ አዳም ወሰናይት ከመ ፀሐይ ብርህት ወከመ መርዐት ስርጉት . . . የክርስቶስ ሀገር፣ እንደ ሙሽራ የተሸለመች፣ ፍፁም ያማረች፣ እንደ ፀሐይ የምታበራ ናት፡፡ በውስጧ የእግዚአብሔር ልጆች ይገባሉ፡፡ በእርሷ ላይ የእግዚአብሔር ምስጋና ያድራል፡፡ ከላይዋ የሕይወት መንፈስ አይጠፋም፡፡ ቅድስት ሀገር ሰላማችን የመለኮት ማደሪያ ትሆነን ዘንድ እርሷን ሰጠን፡፡እንደ ኢየሩሳሌም የንጉስ ከተማ፣ ፍርድ እና ፅድቅ ያለባት፣ የሙሽራ ልዩ ውበት የሁልጊዜ መገለጫዋ የሆነ፣ ፀሐየ ፅድቅ ክርስቶስ ጉልላቷ የሆነ፣ በእርሱ የሚያምኑ ሁሉ በእርሷ ውስጥ በምስጋና ይኖራሉ፡፡ ፆሙን ሁሉ እንዲሁም ከፆሙም ውጪ ቢሆኑም ከእርሷ አይለዩም፡፡ ልጅ ከእናቷ ልትለይ እንዴት ትችላለች? አቤቱ ፀሎታችንን ስማን እያሉ በእርሷ ይማፀናሉ፡፡

 ሃሌ ሃሌ ሉያ እስመ ፅልመትኒ ኢይፀልም በሀቤከ ወሌሊቲኒ ብሩህ ከመ መዐልት በአምጣነ ፅልመታ ከማሁ ብርሀና. . . በአንተ ዘንድ ጨለማ የለም፡፡ ሌሊትም እንደ ቀን ብርሃን ነው፡፡ በአንተ ዘንድ እንደ ጨለማነት ብርሃንነቱም አንድ ነው፡፡ የሀያላን አምላክ አቤቱ ፀሎቴን ስማኝ፡፡ ከህፃንነቴ ጀምሮ ያደረኩትን ሀጢአቴንም በደሌን አቤቱ አታስብብኝ፡፡ሁሉን የምትገዛ አንተ ስለእኛ ብለህ መጣህ፡፡ በዚያ በአንተ ዘንድ ጨለማ የለም፤ ስፍራም የለውም፡፡ ስለዚህ በፅድቅህ ጨለማ ውስጥ ላለነው ለእኛ ድንቅ ብርሃን አንተን ማወቅን ስጠን፡፡ በፆማችን እንደ ነነዌ ሰዎች የቁጣህን መዐት መልስልን፡፡ ስለ ሀጢአታችን እናለቅስ ዘንድ ጥበብ እንዳላቸው እንመላለስ ዘንድ ፆማችንን ባርክልን፡፡ የምንማረው ሁሉ አንተን ወደ ማወቅ ያድርሰን፡፡ ወንበዴው እንኳን በተፈጥሮ ህግ አንተን አውቆህ የለምን?

 ፈያታዊ ዘየማን መኑ መሐረከ ወመኑ ነገረከ ታዕምር. . . የቀኙ ወንበዴ ሆይ! ይህን ታውቅ ዘንድ ማን አስተማረህ? ማንስ ነገረህ? ነቢያትን አልመረመርኩም ሐዋርያትን አልተከተልኩምአላ ፀሐይ ቀፀበተኒነገር ግን ፀሐይ ጠቀሰችኝ እንጂ፡፡ ባየኋት ሰዓት አመንኩ፡፡ የመስቀሉ ኃይል መድኃኒት ሆነኝ፡፡

 እንግዲህ በእርሱ ሰላም የዛሬውን እንፈጽም፡-ስለእኛ ብለህ ነፍስህን የሰጠህ ክርስቶስ ወደ እኛ ተመልከት፡፡ የቃልህን በረከት እንደምናገኝ እናምናለን፡፡ በዚህ ቤት እንዳዘዝከን በሰላም እንወጣ እንገባ ዘንድ፣ ፆምን እንፆም ዘንድ ፈቃድህ ይሁን፡፡ የሰላም እህቷ ፆም ዋጋ አላትና . . . ሙሉ ቀን ላዋልከን ለዚህ ሰዓት ላደረስከን ላንተ ምስጋና ይገባሀል. . . አቤቱ አምላካችን ማረን፡፡ አንተ ከእኛ ጋር ኑር፡፡ ሰላምህን ስጠንአሜን!

 ለእርሱ ልጅነት የማልበቃ ደካማ ስሆን የማይገባኝን ነገር ስለፃፍኩ ስለእኔ ፀልዩልኝ አሜን በጾሙ ሰላምን ይስጠን ጾሙን በሰላም ያስፈጽመን አምላከ ቅዱስ ያሬድ ይጠብቀን፡፡

No comments:

Post a Comment

FeedBurner FeedCount