Friday, March 28, 2014

ደብረዘይት ዘቀዳሚት ሰንበት



በዲ/ን ስመኘው ጌትዬ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ መጋቢት 20 ቀን 2006 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!

 የነፋሳት ሩጫን ያህል የዓይን ጥቅሻም ያህል ከሰዎችና ከመላእክት ዘንድ በአንድነት ለሚሠገድለት ለእርሱ ምሥጋና ይገባል:: ጥንት በሌለው በፊተኛው፣ ፍጻሜ በሌለው በኋለኛው ስም ሰላም ይሁንላችሁ:: (መጽሐፈ ምሥጢር)


 እንደሌላኛው ሳምንት ዛሬም የቅዳሜ ድርሰቱ ከሌሎች ቀናት አጠር ያለች እና ስለመስቀል ክብር የምታወሳ ናት::

ርድአነ በኃይለ መስቀልከበመስቀልህ ኃይል እርዳን፡፡ በጠዋት ከእንቅልፍ ተነስተን እናመሰግንሃለን:: ለአንተ ምሥጋና ይገባል::” በመስቀሉ በኩል ስለተደረገው ሰላም ለሁላችሁ ሰላምታን በንጋት በመስጠት ቅዱስ ያሬድ ይጀምራል::

 በመቀጠል ጉልላቷ መስቀል የሆነች ቤተክርሰቲያንን ይሳለማታል:: “ትብል ቤተክርስቲያን አዋልደ ኢየሩሳሌም ፃኣ ትርዓያቤተክስቲያን አለች፡- የኢየሩሳሌም ልጆች ንጉሣችሁን ታዩ ዘንድ ውጡ:: የእሾህ አክሊል አቀዳጁት፤ በእንጨት ላይ ሰቀሉት፤ በመስቀሉ ሕዝቡን አዳነ::” ደም ግባቱን ደም የሸፈነውን፣ እንደ ነገሥታት የዕንቁ አክሊል ሳይሆን የአዳምን እሾህ በጭንቅላቱ የተሸከመውን፣ ከገነት የሚያወጣ ሳይሆን ወደ ገነት የሚያስገባ እንጨት ላይ መድኃኒትን ያደረገውን ተመልከቱት::

 ሰቀልዎ አይሁድ አፍአ እም ኢየሩሳሌምአይሁድ ከኢየሩሳሌም ዉጭ ሰቀሉት፡፡ ቤተክርስቲያን ግን ኢየሱስን በእንጨት መስቀል ተቸንክሮ አይታ ወደደችው፤ ሰላምም አለችው::” ቤዛ የሆናትን፣ የአካሏን ራስ ለእርሷ ሲል ራሱን በሰጠበት መስቀል አይታው ፍቅሩ ገዛት:: ለእኛ ሲል በተሰቀለበት መስቀል ጌታን በልባችን ማየት ምንኛ መታደል ነው::

 እስመ በመስቀሉ ለክርስቶስ ተሞዓ ሞትበክርስቶስ መስቀል በከበረ ደሙ ሞት ተሸነፈ፤ ጨለማ ተሠደደ፤ ብርሃን ወጣ፤ ሰይጣን ታሠረ፤ ዓለም ተቀደሰ፤ ቤተክርስቲያን ተቀደሰች::… አቤቱ መስቀልህ ለባሪያዎች ነፃነት፣ ለሚያምኑት ሰላም፣ ለሙታን ትንሣኤ፣ በችግር ላሉት ረዳት ለዓለም ሁሉ ብርሃን፣ የቤተክርስቲያን መሠረት ነው::” ስለዚህም ጽዮንን ክበቧት፤ በአዳራሿም በደስታና በሰላም ጸሎታችንን እናቅርብ:: የሰላም አምላክ ሰላሙን ያድለን::

No comments:

Post a Comment

FeedBurner FeedCount