Tuesday, March 11, 2014

ምኩራብ ዘረቡዕ



በዲ/ን ስመኘው ጌትዬ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ መጋቢት 2 ቀን፣ 2006 ዓ.ም.)፡- በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሃዱ አምላክ
 ጸልዩ እምቅድመ ንባበ ዝንቱ ክርታስ

 የሕልውናው መሠረት በማይገኝ፣ በቁጥርም በማይቆጠር፣ የፀሐይን ክበብ በነፋሳት ሠረገላ በሚከምር፣ የመብረቶች ብልጭታ ሲያበራ የነጎድጓድም ድምጽ ሲጮህ የዝናብ ጠብታዎችን ከደመናዎች ማህፀን የሚቀዳ፣ በሥሉስ ቅዱስ ስም በአንዲት ምክርና ንግግር አንድ በሆነ ሥላሴ ሰላም ለሁላችን ይሁን፡፡ ዛሬ አባታችን ቅዱሥ ያሬድ እንደ ትናንትና ባለ አዲስ ምሥጋና ነገም በሚያመሰግንበት በጎ ቃል ቤተክርስቲያንን እያወደሰ እኛን ያስተምረናል፡፡ ከሀያ አራቱ ካህናተ ሰማያት ጋር ያሰልፈን፡፡


 ዛሬ ከሌላው ቀን በተለየ መጨረሻው መጀመሪያ አድርጎ ይጀምራል፡፡ ከዚያ በኋላ ሰላምታውን ይቀጥላል፡፡ውእተ አሚረ ይትወሀቦሙ ካልዕ ልብ ትሠርፅ ሃይማኖትያን ጊዜ ልብ ይሠጣቸዋል፡፡ ሃይማኖት ትሰፋለች፡፡ ሞትም ይሸነፋል፡፡ ጽድቅ ትመጣለች፡፡ ትዕግሥት ይሰበሰባል፡፡ ያን ጊዜ ከእግዚአብሔር ብርሃን እና መብረቅ በቀር ክረምትና በጋ የለም፡፡ ሁሉ የተዘጋጀለትን (የሚጠብቀውን) እስኪያይ ድረስ፡፡አዎን ከእንቅልፋችን በነቃን ጊዜ ያውም በዚህ የጾም ወቅት የመጨረሻውን ዕለት መጀመሪያ እንድናስብ ይነግረናል፡፡ እርሱ ሰው ሞቱን የሚያስብ በመጨረሻው ሰዓት ሰልፉ የት እንደሆነ የሚጨነቅ ልባም ነው፡፡ በዚያች አሥፈሪ ቀን እናት ወይም አባት የለም፡፡ የተማመኑበት ሁሉ አያድንም፡፡ የሠራነው ብቻ ይከተለናል፡፡ ስለዚህ በጾማችን ሁሉ ጠዋት ስንነቃ ይህንን ቀን እያሰብን እንጸልይ፡፡

 በጽባሕ እቀውም ቅድሜከ ወበጽባሕበጠዋት በፊትህ እቆማለሁ፡፡ በፊትህም አንተን በመፍራት እታያለሁ፡፡ ቤተክርስቲያንን እንሳለማት፡፡ ወደ እሷ ለሚገሠግሡ ብርሃን ለጻድቃን ሞገሳቸው ለሚያምኑ ብርሃን ናት፡፡ በሰማይ አምሳል የሆነ ሥራዋ ያማረ ነው” ብሎ ሰላምታውን ሲጨርስ ወደ ውስጥ ዘልቆ ምሥጋናውን ይጀምራል፡፡

 አርእየኒ ገጸከ ወአስምዓኒ ቃለከፊትህን አሣየኝ፡፡ ቃልህን አሰማኝ፡፡ መልካም ነውና፡፡ የመስቀልህ ነገርም እውነት ነው፡፡ በእውነት ተናገርከኝ፡፡ በዕፀ መስቀልህ ያፈራች ቦታ ትሰግድልሃለች፡፡አቤቱ አምላካችን በዚህች ቀን ለቤትህ በጾምና በጸሎት ስንለምንህ የምሕረት ፊትህን አሳየን፡፡ እነዚያ የሚያምሩ የተሠበሩትን የሚጠግኑትን ዛሬ በየትም ልንሰማቸው ያልቻልናቸውን ቃሎችህን በልቡናዬ ጽላት ጻፋቸው፡፡

 ቀዳሚሃ ለጥበብ ወልድየ ፈሪሃ እግዚአብሔር ውእቱልጄ የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው፡፡ ዳግመኛም አባትና እናትህን አክብር፡፡ ወንድምህን እንደ ነፍስ አድርገህ ውደድ፡፡ ብትጾምና ብትጸልይ የወርቅ ጌጥ በአንገትህ ትሾማለህ፡፡ የክብር አክሊል በራስህ ላይ ይሆናል፡፡ በምሥጋናው አዳራሽ አምላክህ በጠራህ ጊዜ ቅዱሳን እጅ ይነሱሃል፡፡ ከሀጢአት ያዳነህ አምላክ ይመስገን ይላሉ፡፡አቤቱ ይህንን ቃል እናስተውል፡፡ የጾምና የጸሎት ጥቅም ምን እንደሆነ እንመልከት፡፡ የክብር ሁሉ ጌጥ ነው፡፡ ከሐጢአት ይጠብቀንም ዘንድ የምንተማመንበት መሣሪያ ነው፡፡ በዚያም በሰማያት ያሉ የእርሱ ምርጦች ስለ እኛ ምሥጋናን ይጨምሩበታል፡፡

 “…አምላከ አበዊነ አቁርር መዓተከየአባቶቻችን አምላክ አቤቱ እንለምንሃለን፤ እንማልድሃለን፡፡ ከእኛ መዐትህን አርቅ፡፡ ለልጅ ልጅ መዐትህን አታድርስ፡፡ የሥጋን ሕግ አንተ ታውቃለህና፡፡ መንፈስ ከወጣ አይመለስምና፤ በሲኦል ኃጢአትን መታመን የለምና፤ ከሞት በኋላ ለሰው ንስሃ የለውምና፤ አቤቱ የሕዝብህን በደል ይቅር በል፡፡ ርስትህን አታጥፋ፤ እኔን ባሪያህንም ወደ አንተ መልሰኝ፤ ምሕረትህ ብዙ ነውና፡፡የይቅርታ አምላክ የጸኑት ሁሉ አምላክ ለንስሃ ጊዜ ስጠን፡፡ ካለፍን በኋላ መመለስ የለምና፤ አቤቱ ያለ ንስሃ አታጥፋን፡፡

 እኔም እነዚህን ጥቂት ቃላት ከእናንተ ጋር እያዜምኩ እንደቆየሁ አሁን ደግሞ ከሊቁ ጋር መርቄያችሁ ልሰናበት፡፡ዕበይሰ ዘበህላዌሁ ትሕትናበአኗኗሩ ከፍ ያለ፣ በትሕትና በፈቃዱ ነው፡፡ ዓለምን የያዘ፣ ስሙም ታላቅ ነው፡፡ እንደ በደለኛ በእንጨትመስቀል ሰቀሉት፡፡ ሱራፌልና ኪሩቤል ይጋርዱታልሰውን የምትወድ ክርስቶስ ሆይ! በሠርክ እናመሰግንሃለን፡፡ ሙሉ ቀን ያዋልከን፣ በማዳንህ አኑረን፡፡ እናገልግልህ፣ እናመስግንህ፣ እንገዛልህ ዘንድ አድለን፡፡ ዛሬም ስምህን ምሕረትህን በህዝብህ ዘንድ ላክ፡፡ የምሥጋና ንጉሥ ማረን የምሕረት አምላክ በረከትን የምትሠጥ ይቅር በለን፡፡ የአብ የወልድ የመፈንፈስ ቅዱሥ ሰላም በእናንተ ላይ ይደር፡፡አሜን!

1 comment:

FeedBurner FeedCount