Wednesday, March 19, 2014

መጻጉዕ ዘሐሙስ



በዲ/ን ስመኘው ጌትዬ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ መጋቢት 10 ቀን፣ 2006 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!

 ክርስቶስ አምላኬና ተስፋዬ ነው፤ እፀ መስቀሉም የሐይማኖቴ በትር ነው፤ የጎኑም መወጋት የጥምቀቴ ሻሻቴ፤ የግርፋቶቹም ደም የበለሳን ቅባቴ ነው:: ሐዋርያቱ በመንገዱ የሚመሩኝ ናቸው:: እመቤቴ ማርያም የመድኃኒቴ በር ናት፤ ክንፎቿ በብር የተሠሩ ጎኖቿም በወርቅ ሐመልማል የተሠሩ ነጭ ወፍ (መጽሐፈ ምስጢር):: በሰላማዊቷ ነጭ ወፍ ሰላምታ ሰላም ይሁንላችሁ::


  አቤቱ ከቅዱሳንህ ጋር የማይጠገብ የምሥጋናህን እንጀራ እንቆርሳለን:: በማለዳም ከቅዱስ ያሬድ ጋር ቤትህን ሰላም ብለን እንጀምራለን:: የሰማዕታት እናታቸው፣ የመላእክት እህታቸው፣ በሰማያት የቅዱሳን ሃገራቸው ሰላም እንበላት ይለናል:: “እምነ በሀ ቅድስት ቤተክርስቲያን” እኛም አልን::

  ነያ ሠናይት ቅድስት ቤተክርስቲያን ዘበእንቲአነ ተሰቅለቤተክርስቲያን ውብ ናት:: ስለ እርሷ የተሰቀለ ክርስቶስ በደሙ አዳናት፤ በመስቀሉ ባረካት::” የወንበዴዎች ቤት ሳትሆን፣ በወርቅ የምትለወጥ ሳትሆን በክቡር አምላክ ደም የተቀደሰች ቤት ናት:: በመስቀሉ ባርኳታልና የእኛም ጸሎት እንደ ቀኙ ወንበዴ መስቀሉ ባለበት ይድረስ::

 አምላክ ዘበአማን ዘይነብር መልዕልተ አርያም ዘሀሎ እምቅድመ ዓለምበላይ በአርያም የሚኖር፣ እውነተኛ አምላክ፣ ዓለም ከመፈጠሩ እና እስከ ዘለዓለም የሚኖር፣ በመጀመሪያ ሰማያትንና ምድርን መፍጠር ያስቀደምህ፣ በሰማይ ጠፈር ፀሐይን የሾምከው፣ በነቢይ እንደተነገረ ጸሎቴ ወደ አንተ ወደ ቅዱስ መቅደስህ ትግባ::” አንተ ብቻህን የማይጠፋ ብርሃን ያለህ ፀሐይ ነህ፤ ያለ ሹመት የጸናህ፣ ሁሉ ሲሻር የምታይ፣ መጀመሪያ መጨረሻ የሌለህ፣ እንደ ፀሐይ መውጫ መግቢያ የሌለህ፣ በሁሉም ያለህ ነህ::

 ብርሃን ትዕዛዝከ ወጽድቅ ስምከትዕዛዝህ ብርሃን፣ ስምህ ጽድቅ ነው:: ከአዳራሽህ ብርሃን ይምጣ::” አንተ ለእኛ ባበራህልን ጊዜ፣ የአንተ ብርሃን ፀሐይ በሕይወታችን በወጣ ጊዜ ሁሉም ነገር ይለወጣል:: ጣፋጭ የሚያረካ ደስታ ይኖረናል::

  ሶበሰ ይሠርቅ ፀሐይፀሐይ በሚወጣበት ጊዜ እኛም በበጎ ምግባር እንደሰት:: ሰላምን ለአሕዛብ አስተምሩ (ስበኩ)::” የአንተ ፀሐይ ሲኖር ህይወታችን ትምህርት ቤት ይሆናል::

  እመሰ ጾምከ ወጸለይከብትጾም፣ ብትጸልይ፣ ከአፍህ ምግብ ብትሰጥ፣ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ይኖራል፤ መሰረትህ አይናወጥም፤ የለመንከውንም ይሰማሃል፤ እውነትም ከፊትህ ይበቅላል::” “ልዑልን መጠጊያ ባደረግን ጊዜ እውነት እንደ ጋሻ ትከበናለች” ይላል ዜመኛው:: ሁልጊዜም ፍቅርን እናብዛ፤ ተፋቀሩ ተፋቀሩ፤ ይህ ሁሉን ያሸንፋል:: ሁሉን በጎ ያጸናዋል:: አንተ የማትተኛ ቸር ጠባቂያችን በማዳንህ አኑረን፤ ስምህንም እንድንጠራ አድለን:: በአንተ ጸንተን እንኖር ዘንድ:: ካልሆነ ግን በራሳችን ከንቱ ነን::

  ሰብእኬ ንሕነ አኮኑ መሬት ከመ ኃሠርእኛ ሰዎች መሬት አይደለንምን? በእሳት ፊት እንዳለ ገለባ በነፋስ እንደሚበተን ጢስ ነን:: አዲስ ባለቤት በመጣ ጊዜ፣ ነፍስንም ነይ ውጪ ባሏት ጊዜ እሳት የሚጠብቀው ሰው ምንድነው?” አምላኬ ሆይ! ቅጣቴን ፈርቼ ሳይሆን በፍቅርህ ድልድይ የእሰቱን ባሕር እንዳልፍ እርዳኝ:: ሰው መሆኔን አንተ ታውቃለህና ክንድህን ዘርጋልኝ፤ በመስቀልህ ኃይል ጎብኘኝ::

 በዝንቱ አምነ ፈያታዊፈያታዊ በዚህ አመነ፤ አይሁዳዊ በዚህ ተሠደደ:: መስቀል የከበረ የሕይወት እንጨት ነው::”

  በመጨረሻም ከሊቁ ጋርአኃውየ ሰላም ለክሙወንድሞቼ ሰላም ለእናንተ ይሁን፤ በሰላምም እጅ እነሳችኋለሁ፤ ዘወትር በጸሎታችሁ ወደ እግዚአብሔር አስቡኝ::” ታላቅ ትህትና:: ይህን ሁሉ ምሥጋና ይህን ሁሉ የቅድስና ሕይወት የሚኖር አባት በጸሎት አስቡኝ ይለናል:: አቤቱ ባንተው ቃል በጸሎትህ በምልጃህ አስበን:: አሜን!

No comments:

Post a Comment

FeedBurner FeedCount