Tuesday, March 18, 2014

መጻጉዕ ዘረቡዕ



በዲ/ን ስመኘው ጌትዬ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ መጋቢት 9 ቀን፣ 2006 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!

 በአካል ሦስት፣ በሕልውና አንድ በሆነ፣ በመመርመር ገንዘብ በማያደርጉት፣ ምድራዊውን ዓለም ፈጥሮ በሚገዛ፣ ለመንግስቱ ምሥጋና ሰማያዊን ዓለም በፈጠረ በእግዚአብሔር ስም የቤተመቅደስን ምሥጋና የወንጌልንም ቁርባን ለእርሱ እናቀርባለን:: ጉልበት ሁሉ በሚሰግድለት በአምላክ ስም ሰላም ለእናንተ ይሁን:: (መጽሐፈ ምሥጢር)


 እንደወትሮው የልዑል ማደሪያ ቤተክርስቲያንን የመንፈስ ቅዱስ አዳራሽ እኛን ቤተክርስቲያንን ሰላም ብሎ በፍጹም ሠላም የዕለቱን ድርሰት ይጀምራል:: “በሀ ንበላ ኲልነ ንሣለማ እምነ ለቅድስት ቤተክርስቲያንሰላም እንበላት፤ እንሳለማት፡፡ ቅድስት ቤተክርስቲያን እናታችን ናት::” ይገርመኛል በዚህ ጾም ስንቶቻችን የምክንያት ገደላችንን የፍቅር ድልድይ ገንብተንበት ከቤተክርስቲያን አዘውትረናል፡፡ አባታችን ግን ሁልጊዜ ጸሎቱን እናቱን እናታችን ቅድስት ቤተክርስቲያን ቀርቦ ሰላም ብሎ ወደ ምሥጋናው ይገባል:: ይህንን ትጋት ያድለን::

  ሐነጽዋ ለቤተክርስቲያን ወሣረርዋ በመንፈስ ቅዱሥ ከመ ትኩን አርአያ ዘበሰማያትቤተክርስቲያንን አነጿት፤ በመንፈስ ቅዱስም አጸኗት፡፡ በሰማያት አርአያ (ምሣሌ) ትሆን ዘንድ፣ ከነደ እሳት ታድነን ዘንድ አረማዊ (የማያምን) ክርስቲያን ይሆን ዘንድ ሠሯት::” የጠፉ ሊመለሱባት፣ የተቅበዘበዙ ሊሰበሰቡባት፣ ያልተወለዱ ሊወለዱባት፣ የተወለዱ ሊያድጉባት፣ ያደጉ ከኃጢአት ከእሳት ሊድኑባት፣ በምድር ቀራጺ ሳይሆን በሰማያዊ ጥበብ ተሠራች:: ስለዚህም ውብ ነች::

   ነያ ሠናይት እንተ እም ኀቤየ ንዒ ርግብየ ጽዮንርግቤ ጽዮን ሆይ! ነይ፡፡ ውብ ነሽ፡፡ ደም ግባቷ ያምራል፤ ቃሏም ይጣፍጣል፡፡ ከተራሮች ራስ ይልቅ ከሩቅ ትታያለች፡፡ ለነገስታት መድኃኒት ናት፡፡ በመንገድ መሪ ትሁነን::” በፍቅር የጣለችን ራሷ ክርስቶስ የሆነ የእኛ አካል ቤተክርስቲያን በሚጣፍጥ ቃሏ ለምሥጋና ትጣራለች:: ሊቁም ከፍቅሯ ጥሪ የተነሳ ወደ እርሷ መሄድን አይታክትም:: እለት እለት በአዲስ ሰማያዊ ዜማ ያመሰግናታል:: ሰላም በሏት፣ እርሷ እንደ ፀሐይ ከሩቅ የምታበራ ነች:: ከተራሮች ከፍ ከፍ የምትል በእውነት ወደ እርሷ ገስግሱ:: ፊቷ ከፀሐይ ይልቅ በራ:: ያለ ፍቅር ወደ እርሷ መቅረብን እንፈራለን:: ፍቅር ግን ጣዕም ያለው ሁሉን የሚገዛ ነው፡፡ ሰላማዊት የሰማዕታት እናት የመለኮት ማደሪያ ናት::

  ሰላማዊት ቅድስት ቤተክርስቲያን እሞሙ ለሰማዕት ምልዕተ ምሕረት ማኅደረ መለኮትቅድስት ቤተክርስቲያን ሰላማዊት፣ የሰማዕታት እናታቸው፣ የመለኮት ማደሪያ ናት፡፡ በጨለማ ውስጥ እንዳለ መብራት ትታያለች፡፡ በእሾህ መካከል እንዳለች የሱፍ አበባ፣ በገነት ውስጥ እንዳለ ሮማን:: ሰላማዊት ቅድስት ቤተክርስቲያን በመንገድ መሪ ትሆነን ዘንድ ያዝናት::”

  ከዚያም ጾምንና የጾምን ጌታ በጸሎትና በምሥጋና በዜማ ማወደስ ይጀምራል:: “ጽድቅ ውእቱ ስምከ ወእሙን ግብርከስምህ እውነት፣ ስራህም የታመነ ነው:: በትዕዛዝህ የሌሊት ንጋትና ማለዳ ተሠራ::” በስሙ ሁሉ ጸና፡፡ በስሙ ስም ተሠጠን፡ ክርስትና፡፡ ስሙን ጠርተን እንድናለን:: ከስም በላይ የሆነ ስም::

 መንክረ ገብሩ አይሁድ ዕፀበ መከሩአይሁድ የሚገርም ስራን ሠሩ፡፡ መጥፎ ነገርን መከሩ፡፡ የሚወዱትን ጠሉ፡፡ በቃሉ የሚያድነውን ሰቀሉ:: እርሱ በመሰቀሉ ለሁሉ አበራ::” እንደ ጧፍ ሲያነዱት ለሁሉ የሚያበራ፣ ሲቀብሩት ለሁሉ ትንሣኤን የሚያበስር ጌታ በአይሁድ ልባችን ውስጥ የፍቅር ብርሃኑን ያበራል::

 ርድአኒ ወአድኅነኒ ወሥመር ብየእርዳኝ፤ አድነኝም፡፡ ቅዱሳን አባቶቼን እንደወደድኻቸው እኔንም ውደደኝ::” አቤቱ በዚህ ጾም ጊዜ ኃይሌንና ብርታቴን መዘንኩት፤ አንተ ካልፈቀድክ በቀር የጾምን ዕለት እንኳን መዋል የማልችል ደካማ ነኝ:: እነሆኀቤከ እግዚኦ አንቃዕዶነ አዕይንተነአቤቱ ወደ አንተ አይናችንን እናንጋጥጣለን:: ልባችንን አነሳን፤ ሕሊናቸንንም ከፍ ከፍ አደረግን::” አንተ እንዳልከን እንኖራለን:: ትዕዛዝህንም እንሰማለን::

 ኀድጉ አበሳ ለቢጽክሙ ከመ ይኅድግ ለክሙ አበሳክሙ አቡክሙ ዘበሰማያትየወንድማችሁን በደል አታስቡ፤ በሰማይ ያለ አባታችሁ በደላችሁን ይቅር እንዲልላችሁ:: እንዳይፈረድባችሁ አትፍረዱ፡፡ የዋሆች ሁኑ፤ የምትሞቱበትን ቀን አስቡ፤ አባታችሁ ይቅር ባይ ነው::”

 እናዚም፤ እንኑር፡፡አስተብቊአክሙ አኃውየ መሃይምናን ታጽንዑ ሃይማኖትክሙየምታምኑ ወንድሞቼ! ሃይማቶታችሁን ታጸኑ ዘንድ ከእርሱ ጋር ፍቅራችሁን ታጸኑ ዘንድ እማልዳችኋለሁ:: በጎ ስራን ሥሩ፤ ክርስቶስ ባለበት በሱ ኑሩ፤ ደስታና ሰላም በመካከላችሁ ይብዛ፤ መዝሙርን አንብቡ፤ በተቀደሰ ማሕሌት እግዚአብሔርን አመስግኑ:: …የሰላም አምላክ ሰይጣንን ፈጥኖ ከእግራችሁ በታች ጥሎ ይቀጥቅጠው፤ የጠራችሁ ሰላምን ይስጣችሁ፤ የሰላም አምላክ ከእናንተ ጋር ይሁን::” አሜን!

No comments:

Post a Comment

FeedBurner FeedCount