Wednesday, March 5, 2014

ቅድስት ዘሐሙስ


በዲ/ን ስመኘው ጌትዬ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ የካቲት 26 ቀን 2006 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሃዱ አምላክ

ጸልዩ እምቅድመ ንባበ ዝንቱ ክርታስ

 ምህረቱን በማንለካው የልብ ጥልቁን በሚያውቀው በብላቴና ድንግል ማህፀን ባደረው የፀሐይ ብርሃን በእርሱ ፊት ጨለማ በሆነ ሰሜንና ደቡብ ምስራቅና ምዕራብ መስዕ እና አዜብ ሳይታወቅ አስቀድሞ በነበረ የፀሐይና የጨረቃን ክበብ እንደ መስታወት በወሰነ ለብርሃናት ጌታቸው በሚሆን በቤተ መቅደሱ በመገናኛው ድንኳን በጥምቀቱ የተወለዳችሁ ሁሉ ከዓለም በሚለየው የጌታ ሰላም ለእናንተ ሰላም ይሁን፡፡ ከኮከብ ለምትበራ፣ ከተራሮች ሁሉ ከፍ ከፍ ላለችው፣ ብርሃኗ የእውነት ፀሐይ ለሆነው ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን በሚያቀርበው ውዳሴ እና የፆምን ነገር ከሊቁ ጋር እያወደስን እየተማርን እንቆያለን፡፡


 ዜመኛውእግዚአብሔር ብርሃኔ እና መድኃኒቴ ነው ምንስ ያስፈራኛል” ብሎ ይጀምራል፡፡ ሁሉን የሚችለው የቤተ ክርስቲያን አምላክ ከእኔ ጋር ነውና ክፉን መፍራት የእኔ አይደለም፡፡ የነፍሴን አውሎ ነፋስ የሚያቆመው ስለ ሁሉ ማመስገን ጀመርኩ፤ የእርሱን ማደሪያ ቤቱን እቀድሳለሁ፡፡

እንተ ተሀንፀት በስሙ ወተቀደሰት በደሙ ወተዐትበት . . . በስሙ የተመሰረተች የሆነች በደሙ የተቀደሰች በዕፀ መስቀሉ የተባረከች ፅዮን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የቅዱሳን መዓዛቸው ንፁህ አዳራሽ ነፃ የምታወጣ ምስጋና የከበባት ናት፡፡ ቅድስት ፅዮንን ተመልከቷት ሙሴ በደብረሲና አያት ነቢያት እና ሐዋርያት ሁሉ ተመለከቷት፡፡ስሙን ስም አድርጎላት የእኛ ቤት አሰኛት፡፡ በእንጨት አልሰራትም፤ በእንቁም አላነፃትም፤ በደሙ ፈሳሽነት ቀድሶ ሰጠን እንጂ፡፡ በመስቀሉ ባርኮትን አደላት፡፡ ስለዚህም የመጽናኛችን ከተማ ንፁህ አዳራሻችን አደረጋት፡፡ ነፃነታችንን በእርሷ እንሰበካለን፡፡ የመልካም ሽቶአችን ምንጭ ናትና፡፡

 ዕዝራኒ ርዕያ ከመ ብዕሲት ህዝንት . . . ስለ ልጆቿ እንዳዘነችና እንደተከዘች ሴት ስታለቅስ ባያት ግዜ እዝራ ተናገራት፤ እንዲህም አለ፡- ይህች ቤታችን ማደሪያችንም ናትና ስለ ፅዮን እኛ እንተክዝ፤ ካህናቶቻችን ተገድለዋል፤ አባቶቻችንም የሰሩት መስዋእት ተወስዷል፡፡ ይህንን ሲናገር የሚያስፈራ የእግዚአብሔር ምስጋና በእርሷ ላይ አየ፤ ድንገት ገጿ እንደ ፀሐይ በርቷልና ደነገጠ፡፡ ወደ እርሷ መቅረብን ፈራ፡፡ቅዱሱ ሊቅ በእውነት ስለ እዝራ አልተናገረም፤ ስለምትመጣው ቤተ ክርስቲያን እንጂ፡፡ ቃሉን ካስተዋልነው በሴት አምሳል ስለ ልጆቿ የምታለቅሰው ዛሬ ማን ናት? ስለ ካህናቶቿ የተከዘችው ማን ናት? ስለ ፍቅር መስዋዕቱ መጉደል የተከዘችው ማን ናት? እርሷ ስለ ልጆቿ ኃጢያት የምታለቅስ ስለ ካህናቶቿም የምታስብ ስለ ፍቅር የምትቃጠል የምስጋናው አበባው ፍሬ የሚሆነባት ይልቁንም እነዚህ ሁሉ በፆሙ አንድ ሆነው በፍቅር ማየት የምትፈልገው ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡

 ሊቁ ወድሶታውን በቤቱ ቀጥሏል፡፡አንተ ውእቱ ክብርነ . . . ክብራችን አንተ ነህ፤ የተገባኸን አንተ ነህ፡፡ የመድኃኒታችን አክሊል አንተ ነህ፡፡ ፀሐይን የምታወጣ አንተ ነህ፡፡ ሰላምን የምትሰጥ አንተ ነህ፡፡ የነድያንን ነፍስ ደስ ታሰኛለህ፡፡አቤቱ አንተን ማመስገን ኑሮአችን አድርግልን፤ የሁሉ ጌታ ሁሉን የምታደርግ አንተ ነህና ፆማችንን ለአንተ ንፁህ መስዋእት አድርግልን፡፡

 ናሁ ትህትና ይደሉ . . . አሁን ትህትና ይገባል፤ ልንገዛ ራሳችንንም ዝቅ ልናደርግ ይገባል፡፡ ወርቅን አትውደዱ፤ ወርቅስ ከንቱ ነው፡፡ ልብስም ያረጃል፤ በፆምና በፀሎት ከሞት ይድናሉ፡፡ በምፅዋትም ሀጢአት ይሰረያል፡፡ ትህትና እንደሚገባ ሌላ አይገባም፤ እንደ እውቀት የሚገባ ነገር የለም፡፡በዚህ ላይ እኔ ምን እላለሁ? ግን ዜማውን ልቀጥል፡-ቀጸበቶ ለፈያታይ . . . ወንበዴውን ፀሐይ ጠቀሰችው፤ በእውነት ወንበዴው ነገረ መስቀልህ የተረዳ እንደሆነ አመነ፡፡ አቤቱ እኔንም ቃልህን አሰማኝ፡፡በሀጢአት የኖርኩ እኔንም ዛሬ በቀኝህ እንድሰቀል አድርገኝ፡፡ በዚያም ያንተን የደስታ እና የምስራች ቃል ያንተን የገነት ግብዣ እሰማ ዘንድ እፈቅዳለሁና፡፡ በዚያም ባልሆን ዛሬ በዚህ በፆም ትባርከኛለህ፡፡

 ንፁም ፆመ ወናፍቅር ቢፀነ ወናዕትት . . . ፆምን እንፁም፤ ወንድማችንን እንውደድ፡፡ ከልባችን ክፉን እናስወግድ፤ ያን ጊዜ አባታችን በፍጥነት ይሰማልና፡፡የልባችንን ምኞት የዚህ ዓለም እሾህ ባረምን ጊዜ ፀሎታችን የተሰማ ይሆናል፡፡

 “. . . እስመ ፆም ዐቢይ በቁዔት . . . የፆም ጥቅም ታላቅ ነው፤ ነፍሳችሁን ከኃጢአት ነፃ ታደርጋለች፡፡ ለወጣቶችም ፅሙናን ታስተምራለች፡፡ ይህች ቅድስት ፆም ሰላምን ታፈራለች፡፡ ደስታንም ትከፍላለች፡፡በፆም የተገታ ስጋ በድካሙ ፅሙናን ይማራል፡፡ በተለይም ሁሉን ማድረግ የሚፈልገው የወጣቶች ስጋ በፆም ልጓምነት ከሀጢአት ጋር መዋጋትን ይለማመዳል፡፡

 ኢትኮንኑ ከመ ኢትትኮነኑ . . . እንዳይፈረድባችሁ አትፍረዱ፤ እንደ አባቶቻችሁ የዋሀን ሁኑ፡፡ የሞታችሁን ቀን አስቡ፡፡በፆም የሰው ልጅ ሀጢአት ላይ እንጂ ስጋዊና ደማዊ የሆነ ሰው ላይ አይፈርድም፤ እንዲያ ከሆነ ግን በራሱ ላይ ፍርድን ፍህምንም ያከማቻል፡፡

  ይህችን ጥቂት ቃላት ከአባታችን ጋር እንድናይ የፈቀደልን አምላክ ይመስገን፤ በእርሱ በሊቁ ምርቃት እሰናበታችኋለሁ፡፡አምላከ ሰላም ይቀድሰክሙ ወያጥኢክሙ ነፍሰክሙ - የሰላም አምላክ ይቀድሳችሁ ነፍሳችሁንም ፍፁም ጤና ይስጣት፡፡
ለእርሱ ልጅነት የማልበቃ ደካማ ስሆን የማይገባኝን ነገር ስለፃፍኩ ስለእኔ ፀልዩልኝ አሜን በጾሙ ሰላምን ይስጠን ጾሙን በሰላም ያስፈጽመን አምላከ ቅዱስ ያሬድ ይጠብቀን፡፡

No comments:

Post a Comment

FeedBurner FeedCount