Wednesday, September 25, 2013

ነገረ መስቀል

(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፥ መስከረም ፲፮ ቀን፥ ፳፻፮ ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሓዱ አምላክ አሜን!!!
በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ. ሥርዓት መሠረት ከመስከረም ፲ እስከ መስከረም ፳፭ ያለው ሳምንት “ዘመነ መስቀል” ይባላል፡፡ በዚህ ሳምንት ስለ መስቀል ክብር ይነገራል፤ መዝሙረ መስቀልም ይዘመራል፡፡ መስቀል ማለት “ሰቀለ” ከሚል የግእዝ ግሥ የተገኘ ሲኾን ትርጓሜውም “የተመሳቀለ፣ መስቀለኛ” ማለት ነው፡፡
 መቅድመ ወንጌል እንደሚነግረን፥ አዳም የማይበላውን በልቶ ከእግዚአብሔር አንድነት ከተለየ በኋላ አብዝቶ ያለቅስ ነበር፡፡ በኀጢአቱ ከማዘንና ከማልቀስ በቀርም ሌላ ግዳጅ አልነበረውም፡፡ በልብ መታሰቡ በቃል መነገሩ ከፍ ከፍ ይበልና ብዙ መጨነቁን፥ ጸዋትወ መከራዉን ያየው ቸሩ እግዚአብሔር ግን አዘነለት፡፡ “እቤዝወከ በመስቀልየ ወበሞትየ - በመስቀሌና በሞቴ አድንኀለኹ” ብሎም ቃል ኪዳን ገባለት /ኪዳነ አዳም ፫፡፫-፮፣ ዘፍ.፫፡፲፭/፡፡ መጽሐፈ ቀሌሜንጦስ እንደሚነግረንም ከ፭ ቀን ተኵል በኋላ እንደሚያድነው ተስፋ ሰጠው፤ ከ፭ ሺሕ ፭ መቶ ዓመታት በኋላ ሲል ነው፡፡ “ነገረ መስቀል” የምንለውም ይኸው ለአዳም የተሰጠው ተስፋ ነው፡፡

Friday, September 13, 2013

የኢትዮጵያ የዘመን አቈጣጠር - ክፍል 3 (የመጨረሻው ክፍል)



ገ/እግዚአብሔር ኪደ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፥ መስከረም 3 ቀን፥ 2006 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡
 በዚህ ክፍል በአንዳንድ ምእመናን የሚጠየቁትን አንዳንድ ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት እንሞክራለን፡፡
 ጥያቄ አንድ፡ - የኢትዮጵያ የዘመን አቈጣጠር ከአውሮፓውያን የዘመን አቈጣጠር ስለምን 7 ወይም 8 ዓመት ወደኋላ ይዘገያል?

Tuesday, September 10, 2013

የኢትዮጵያ የዘመን አቈጣጠር - ክፍል 2

ገ/እግዚአብሔር ኪደ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፥ መስከረም 1 ቀን፥ 2006 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡

ዐውደ ዓመት
  ዐውደ ዓመት ማለት በፀሐይ 365¼ ዕለት፥ በጨረቃ 354 ዕለት ነው፡፡ ከፀሐይ ወሮች ዐጽፈ አውራኅ፥ ከጨረቃ ወሮች ደግሞ ሕጸጸ አውራኅ ይገኛል፡፡ ዐጽፈ (ድርብ፣ ዕጥፍ) አውራኅ ማለት በየወሩ 30 ቀን በሱባኤ ሲቀመር (ለሰባት ሲከፈል) የሚቀረው 2 ቀን በሌላው ወር ተደምሮ የሚቈጠር ስለሆነ ነው፡፡ ጨረቃ በዕለት፣ በ15 ቀን፣ በወርና በዓመት የምታጐድለው ቀንና ሰዓት ሕጸጽ ይባላል፡፡ ለምሳሌ በፀሐይ አቈጣጠር አንድ ወር 30 ቀን ሲሆን በጨረቃ ግን አንዳንዴ 29 ይሆናል፡፡ ይህ ጨረቃ ከፀሐይ የምታጐድለው አንድ ቀን ነው ሕጸጽ እያልነው ያለነው፡፡ ስለዚህ በፀሐይ አቈጣጠር ዐዲስ ዓመት መስከረም 1 ሲሆን በጨረቃ አቈጣጠር ግን ነሐሴ 24 ወይም ነሐሴ 25 ይሆናል ማለት ነው፡፡ [ጨረቃ ለ6 ወራት 29፣ 29 ትሆናለች፡፡ ስለዚህ 6 ቀን ታጐድላለች ማለት ነው፡፡ 5 የጳጉሜንን ዕለታትንም ጨምራ ስታጐድል በጠቅላላ 11፥ በየአራት ዓመት ደግሞ 12 ቀናት ታጐላለች፡፡ በዚህም ምክንያት በጨረቃ አቈጣጠር ዐዲስ ዓመት ነሐሴ 24 ወይም በየአራት ዓመት ነሐሴ 25 ይሆናል ማለት ነው፡፡]

የኢትዮጵያ የዘመን አቈጣጠር - ክፍል 1

ገ/እግዚአብሔር ኪደ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፥ ጳጉሜን 5 ቀን፥ 2005 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡

መግቢያ

  የሰው ልጅ ሕይወት ከጊዜ ጋር በእጅጉ የተቈራኘ ነው፡፡ እያንዳንዱ ማኅበረሰብም የራሱ የሆነና ይህን ከሕይወቱ ጋር የተቈራኘውን ጊዜ የሚቀምርበት የዘመን አቈጣጠር አለው፡፡ ሊቃውንት ሲናገሩ “ለቃለ እግዚአብሔር ጥናት ሰዋስው፥ ለምስጋና ዜማ፥ ለምሥጢራት ቀኖና እንደሚያስፈልግ ሁሉ ለጌታ በዓላትም ባሕረ ሐሳብ የግድ ያስፈልጋል” ይላሉ፡፡ ኢትዮጵያም የራሷ የሆነ ሐሳበ ዘመን ማለትም የዘመን አቈጣጠር አላት፡፡ ይህ የዘመን አቈጣጠር (ሐሳበ ዘመን) የዘመናት፣ የዓመታት፣ የወራት፣ የሳምንታት፣ የዕለታት፣ የሰዓታት፣ የደቂቃዎች፣ የቅጽበትና (የካልዒትና) የመሳሰሉት ጊዜያት በሐሳብ የሚመዘኑበት፣ የሚሰፈሩበት፣ የሚቈጠሩበት ምድብና ቀመር ተሰጥቶአቸው የሚገኙበትን ውሳኔና ድንጋጌ እያሰማ የሚጠራበት ትምህርታዊ ውሳኔ ነው፡፡

Wednesday, September 4, 2013

« ርኢኩ ሰብዐተ መላእክተ እለ ይቀውሙ ቅድመ እግዚአብሔር » ራዕ 8÷2


                                                                             በክፍለ ሥላሴ 

(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ጳጉሜ 1 ቀን፣ 2005 ዓ.ም.)፡-  በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡
መግቢያ
     ቅዱስ መጽሐፋችን «የእግዚአብሔር ቃል ሁሉ ተፈትናለች፣ እርሱ ለሚታመኑት ጋሻ ነው፡፡ እንዳይዘልፉህ ደግሞም ሐሰተኛም እንዳትሆን በቃሉ አንዳች አትጨምር» (ምሳ.30÷6) ይላል፡፡ ሰማያዊውን ወንጌል ቅዱሱን የእግዚአብሔር ቃል መንፈሳውያን በመንፈስ ቅዱስ ኃይል መሪነት መረመሩት፣ አመኑት አልፈውም ታመኑበት የጠላትን የክህደት ጦር ይመክቱበት ዘንድ ጋሻ ሆናቸው፡፡ ፈቃዳቸው እና የልባቸውም ሃሳብ የሚመራቸው ግን በገዛ መንገዳቸው ቃሉን ፈትነው የተከደነውን ሊገልጡ የተሰወረውን ሊያወጡ ቢባዝኑ ጥርጣሬን ጸንሰው ክህደትን ይወልዳሉ፣ ሀሰትን ጨምረው ተዘልፈው ይጠፋሉ፡፡ «ወንጌላችን የተከደነ ቢሆን እንኳ የተከደነባቸው ለሚጠፉት ነው»  (1ቆሮ 4÷3)፡፡

“ይህን ብታውቁ፥ ብታደርጉትም ብፁዓን ናችሁ” - የዮሐንስ ወንጌል የ48ኛ ሳምንት ጥናት (ዮሐ.13፡1-19)

ገ/እግዚአብሔር ኪደ

(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፥ ነሐሴ 29 ቀን፥ 2005 ዓ.ም.)፡- የነገረ መለኮት ሊቃውንት እንደሚያስተምሩት ከዚህ ከ13ኛው እስከ 17ኛው ምዕራፍ ያሉት የዮሐንስ ወንጌል ምዕራፎች ጌታችን በምሴተ ሐሙስ ያደረጋቸውን የፍቅር ድርጊቶችንና ትምህርቶቹን አጠቃልለው ስለያዙ “የፍቅር ወንጌል” ብለው ይጠሩዋቸዋል፡፡ በእነዚህ ምዕራፎች ብቻ ወንጌላዊው “ፍቅር” እያለ 20 ጊዜ ጽፏል፡፡ የፍቅር ግብር ምሥጢረ ትሕትና የበለጠ የተገለጠው በዚህ ዕለት ነው፡፡ የፍቅር ማዕድ ምሥጢረ ቁርባን የተመሠረተው በዚህ ዕለት ነው፡፡ የምሥጢረ ጸሎት ትምህርትም በስፋት በጌቴ ሴማኒ የአታክልት ስፍራ የተማርነው በዚህ ዕለት ነው፡፡  እኛም ለዛሬ ከወንጌላዊው ጋር በሕፅበተ እግር ስለተገለጠው ስለ ምሥጢረ ትሕትና እንማማራለን፡፡ ምሥጢሩን ይግለጥልን!

Thursday, August 22, 2013

ድንግልማ በእውነት ተነሥታለች - በዲ/ን ብርሃኑ አድማስ ለተሐድሶዎች የተሰጠ ምላሽ

(መቅረዝ ዘተዋሕዶ ነሐሴ ፲፮ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም)፡- እንኳን ለእመቤታችን በዓለ ዕርገት አደረሳችሁ፡፡

ዘሰ ይብል አፈቅረከኪ ወኢያፈቅር ተአምርኪ [ትንሣኤኪ ወዕርገትኪ] ክርስቲያናዊ፤
ኢክርስቱን ውእቱ አይሁዳዊ ወሠርፀ እስጢፋ ሐሳዊ፤
አንሰ እቤ በማኅሌተ ሰሎሞን ሰንቃዊ፤
አፈቅሮ ለፍግዕኪ ወለተ ይሁዳ ወሌዊ፤
ከመ መርዓቶ ያፈቅር ጽጌኪ መርዓዊ፡፡

Tuesday, August 20, 2013

ሥጋ ሥጋት ሲኾን

በዲ/ን ብርሃኑ አድማስ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ ነሐሴ ፲፬ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም)፡- ከኢትዮጵያ ውጭ ለመኖር በኹኔታዎች ተገድዶ ወደ ጀርመን የሔደ አንድ ወንድማችን በሚኖርበት ሀገር እጅግ በሽተኛ ኾኖ ይቸገራል፡፡ ጾም አይጾም፤ ምግብ አይመርጥ የነበረው ሰው የፈለገውን ቢያደርግም ለጤናው ሽሎት ያጣል፡፡ በሚኖርበት ሀገር በሕክምና ዕውቀት በጣም ያደገ ስለነበር እጅግ ብዙ ሙከራዎችን ቢያደርግም ተስፋ ያጣል፡፡ በመጨረሻ በአመጋገብ ብቻ ሕክምና ወደምታደርግ ስፔሻሊስት ሐኪም ይላካል፡፡ ሐኪሟም የበሽተኛውን የሕማም ታሪክ ጊዜ ወስዳ በተደጋጋሚ ካጠናች በኋላ ሕክምናውን ለመጀመር ኹለት ዝርዝሮች አዘጋጅታ ጠበቀችው፡፡ ከዝርዝሮቹ አንደኛው ሊመገባቸው የሚገባውን የምግብ ዐይነቶች የያዘ ሲኾን ኹለተኛው ደግሞ ሊመገባቸው የማይገባውን የያዘ ነበር፡፡ ዝርዝሩን ይዞ ወደ ቤቱ በመሔድ በትእዛዙ መሠረት መዳኑን እየተጠባበቀ መመገብ ጀመረ፡፡ ለውጡን በመጠኑ እያየ ደስ እያለው ሳለ እንዲበላቸው የታዘዛቸው ምግቦች ቀደም ብሎ በብዛት ከሚመገባቸው የተለዩ ስለነበሩና ቀድሞ በብዛት ይመገባቸው የነበሩት ደግሞ ከተከለከላቸው ውስጥ ስለነበሩ ኹኔታዉን ደጋግሞ ሲመለከት አንድ ነገር ይከሰትለታል፡፡ የተከለከላቸው ምግቦች በሙሉ ሲያያቸው በሀገር ቤት በፍስክ የሚበሉት ሲኾኑ እንዲመገባቸው የታዘዙለት ደግሞ በሙሉ የጾም ምግብ ከሚባሉት ኾነው ያገኛቸዋል፡፡ በኹኔታው በጣም ከተገረመ በኋላ “የጾም ምግብ ለጤና ተስማሚ ከኾነ ለምን አልጾምም?” ይልና ፈጽሞ ረስቶት የነበረውን ጾም ድንገት በሰኔው የሐዋርያት ጾም ይጀምራል፡፡ ልክ አንድ ሳምንት ከጾመ በኋላ ኹል ጊዜም እንደሚያደርገው ለክትትል ወደ ሐኪሙ ያመራል፡፡ የላባራቶሪ ውጤቶቹ ሲመጡ በተለይ እነ ደም ግፊት፣ ስኳርና የመሳሰሉት በሽታዎች በከፍተኛ ኹኔታ ቀንሰዋል፡፡

Saturday, August 17, 2013

የእሑድ ውዳሴ ማርያም ትርጓሜ

ገ/እግዚአብሔር ኪደ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ ነሐሴ ፲፪ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም.)፡-  በዚህ ዕለት እመቤታችን ከወትሮው ይልቅ ቀደም ብላ መጥታለች፡፡ “ዛቲ ዕለት ተዓቢ እምኩሎን ዕለታት፤ ወውዳሲያቲሃኒ የዓብያ እምኵሉ ውዳሴያት - ከዕለታት ኹሉ ይህቺ ዕለት ታላቅ ናት፤ ከውዳሲያቱም ኹሉ የዚች ዕለት ውዳሴ ታላቅ ነው” አለችውና ባረከችው፡፡ እርሱም በቤተ መቅደስ ባሉ ንዋያት ማለትም፡- በመሶበ ወርቅ፣ በተቅዋመ ወርቅ፣ በማዕጠንተ ወርቅ፣ በበትረ አሮን እየመሰለ ሲያመሰግናት አድሯል፡፡

Friday, August 16, 2013

የቅዳሜ ውዳሴ ማርያም ትርጓሜ

ገ/እግዚአብሔር ኪደ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ ነሐሴ ፲፩ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም.)፡- በዚህም ቀን እመቤታችን ትመጣለች፤ የብርሃን ድባብ ይዘረጋል፤ የብርሃን ዙፋን ይነጠፋል፡፡ ከዚያ ላይ ኹናም ሊቁን ባርካው ምስጋናዉን ጀምሯል፡፡
፩. ንጽሕት ነሽ፤ ብርህት ነሽ፡፡ በአፍአ በውስጥ ንጽሕት ነሽ፡፡ ሊቁ “ዲያተሳሮን” በተባለው የወንጌል ትርጓሜ መጽሐፉ የእመቤታችንን ንጽሕና ሲናገር፡- “የማርያም ሰውነት የምድር ላይ መቅደስ ነው፡፡ በዚሁ መቅደስም ከእግዚአብሔር ዘንድ የተላከ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል በኀጢአት፣ በሞትና በርግማን ፈንታ የበረከትን ዘር ሊዘራ መጣ፡፡ የኤልሳቤጥም ሰላምታ ይህንን አረጋገጠ፡፡… አንተና እናትህ ብቻ በማንኛውም ረገድ ንጹሐን ናችሁ፡፡ ጌታ ሆይ! በአንተ ውስጥ ምንም ነቅዕ የለም፤ በእናትህም ውስጥ ምንም ምልክት የለም” ብሏል /St. Ephrem the Syrian, Commentary on Tatian’s Diatesaron, pp 91-92/፡፡

Thursday, August 15, 2013

የዓርብ ውዳሴ ማርያም ትርጓሜ

ገ/እግዚአብሔር ኪደ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ ነሐሴ ፲ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም)፡- ይህ ዕለት ለምስጋና አምስተኛ ለፍጥረት ስድስተኛ ቀን ነው፡፡ በዚህም ቀን እመቤታችን ትመጣለች፤ የብርሃን ድባብ ይዘረጋል፤ የብርሃን ዙፋን ይነጸፋል፡፡ ከዚያ ላይ ኹናም ሊቁን ባርካው ምስጋናዉን ጀምሯል፡፡ ከወትሮ ይልቅም ደናግልን አስከትላ መጥታለች፡፡

Wednesday, August 14, 2013

የሐሙስ ውዳሴ ማርያም ትርጓሜ

ገ/እግዚአብሔር ኪደ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ ነሐሴ ፱ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም)፡- ይህ ዕለት ለምስጋና አራተኛ ለፍጥረት አምስተኛ ቀን ነው፡፡ በዚህም ቀን እመቤታችን ትመጣለች፤ የብርሃን ድባብ ይዘረጋል፤ የብርሃን ዙፋን ይነጸፋል፡፡ ከዚያ ላይ ኹናም ሊቁን ባርካው ምስጋናዉን ጀምሯል፡፡ ከወትሮ ይልቅም ነቢያትንና ሐዋርያትን አስከትላ መጥታለች፡፡

Tuesday, August 13, 2013

የረቡዕ ውዳሴ ማርያም ትርጓሜ

ገ/እግዚአብሔር ኪደ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ ነሐሴ ፰ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም.)፡-  ለምስጋና ሦስተኛ፣ ለፍጥረት አራተኛ ቀን በሚኾን በዚህ ዕለት ከወትሮ ይልቅ መላእክትን አስከትላ እመቤታችን ትመጣለች፤ የብርሃን ድባብ ይዘረጋል፤ የብርሃን ምንጻፍ ይነጸፋል፡፡ ከዚያ ላይ ኾናም፡- “ሰላም ለከ ኦ ፍቁርየ ኤፍሬም” ትለዋለች፡፡ እሱም ታጥቆ እጅ ነሥቶ ይቆማል፡፡ ከባረከችው በኋላም ምስጋናዋን “ኵሉ ሠራዊተ ሰማያት ይብሉ ብፅዕት አንቲ…” ብሎ ይጀምራል፡፡

Monday, August 12, 2013

የማክሰኞ ውዳሴ ማርያም ትርጓሜ

ገ/እግዚአብሔር ኪደ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ ነሐሴ ፯ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም)፡- ለምስጋና ኹለተኛ፣ ለፍጥረት ሦስተኛ ቀን በሚኾን በዚህ ቀንም እመቤታችን ትመጣለች፤ የብርሃን ድባብ ይዘረጋል፤ የብርሃን ምንጻፍ ይነጸፋል፡፡ ከዚያ ላይ ኾናም፡- “ሰላም ለከ ኦ ፍቁርየ ኤፍሬም” ትለዋለች፡፡ እርሱም ታጥቆ እጅ ነሥቶ ይቆማል፡፡ ክርክር በዕለተ ሰኑይ አልቋልና “ባርክኒ” ብሎ ተባርኮ “አክሊለ ምክሕነ” ብሎ ምስጋናውን ይጀምራል፡፡

Sunday, August 11, 2013

ሠለስቱ ደቂቅን ያዳናቸው ማን ነው ?

በዲ/ን ብርሃኑ አድማስ

(መቅረዝ ዘተዋሕዶ ነሐሴ ፮ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም)፡- ሰኮናቸው ያልተሰነጠቀና የማያመሰኩ እንስሳት (የዘመናችን ተሐድሶዎች)(የመጨረሻ ክፍል)

“ታዲያ ሠለስቱ ደቂቅን ያወጣቸው ማን ነው?” ለሚለው የተሐድሶዎች ጥያቄ የቀረበ መልስ፡፡ 

መጀመሪውንም መጽሐፍ ቅዱሱ ገብርኤል ነው አይልም፡፡ መጽሐፍ ቅዱሱ የሚለው የሚከተለውን ነው፤ ‹‹ የዚያን ጊዜም ንጉሡ ናቡከደነፆር ተደነቀ ፈጥኖም ተነሣ አማካሪዎቹንም፤ ሦስት ሰዎች አስረን በእሳት ውስጥ ጥለን አልነበረምን? ብሎ ተናገራቸው። እነርሱም፦ ንጉሥ ሆይ፥ እውነት ነው ብለው ለንጉሡ መለሱለት። እርሱም፦ እነሆ፥ እኔ የተፈቱ በእሳቱም መካከል የሚመላለሱ አራት ሰዎች አያለሁ፤ ምንም አላቈሰላቸውም የአራተኛውም መልክ የአማልክትን ልጅ ይመስላል ብሎ መለሰ ›› /ዳን 3 24 -25/ ፡፡ በዚህ ገለጻ መሠረት አራተኛውን ያየው ንጉሡ ናቡከደነጾር ነው፡፡ እርሱም አየሁ ያለው አራተኛ ሰው ነው፡፡ የጨመረበት ቢኖር አራተኛው የአማልክትን ልጅ ይመስላል የሚለውን ነው፡፡ ለመሆኑ አራተኛውን ሰው እርሱ ብቻ ለምን አየ ? ሌሎቹ ለምን አላዩም ? አንደኛው የጥያቄው ቁልፍ ምስጢር ያለው እዚህ ላይ ነው፡፡ እውነቱን ለመናገር ይህ ሰው ጥንቱንም ሠለስቱ ደቂቅን ወደ እሣት የጣለው ራሱን ምስል አቁሞ ለምስሉ ሕዝቡን በማሰገድ ራሱን አምላክ አድርጎ ሊያስመልክ ነበር፡፡ ታዲያ ራሱንና እርሱን የመሰሉትን አምላክ አድርጎ የሚቆጥር ከሆነ የሚያየውን አራተኛውን  ሰው ‹‹ የእኛን ልጅ ይመስላል ወይም እኛን ይመስላል›› ለምን አላለም? ከዚያ ይልቅ አርቆ ሌሎች አማልክትን የሚያመልክ አስመስሎ ‹‹ የአማልክትን ልጅ›› ይመስላል ያለበት ምስጢር ምንድን ነው ? ይህን ያለበት ምክንያቱ ያየው ነገር አራተኛው አካል ከህልውና ያለው በዘር በሩካቤ የተወለደ ሰው እነርሱ ሳያዩት እሳቱ ውስጥ ገብቶ ሳይሆን ነገሩ መገለጥ ስለሆነ ነው፡፡

FeedBurner FeedCount